የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የአገልግሎት ጥራት ማሽቆልቆል አሳሳቢ ሆኗል

መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአዲስአበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በታሪኩ አይቶ የማያውቀው የአገልግሎት አሰጣጥ መጨናነቅ እንዳጋጠመውና በዚህም ምክንያት ከዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አንጻር የአገልግሎት ጥራቱ ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱን አንድ ከድርጅቱ የተገኘ ጥናታዊ ጽሁፍ አመለከተ፡፡

አዲሱ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ለሃያ ዓመታት በዓመት 6 ሚሊየን መንገደኞችን በብቃት ሊያስተናግድ ይችላል ተብሎ የተገነባ ቢሆንም በአስረኛ ዓመቱ የመንገደኞች ቁጥር ከ6.5 ሚሊየን በላይ በመድረሱ በኤርፖርቱ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሮአል፡፡

በኤርፖርቱ የሚስተናገዱ አውሮፕላኖች ቁጥርም ባልተጠበቀ ሁኔታ ሲጨምር እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ2001 በዓመት 9 ሺህ 609 ያህል አውሮፕላኖች ሲስተናገዱ፣  በ2012 ወደ 65 ሺህ 417 አውሮፕላኖች ተስተናግደዋል።  የመንገደኞች ቁጥርም በተመሳሳይ ዓመት ከ1.3 ሚሊየን ወደ 6.34 ሚሊየን ከፍ ብለአል።

በአየር ማረፊያው የሚስተናገደው የዕቃ ብዛትም ከ6 እጥፍ ባላይ መጨመሩን መረጃው ጠቁሞ ይህ የመጨናነቅ ችግር ካልተፈታ የኤርፖርቱ አገልግሎት ደረጃው ዝቅ እንደሚልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተመራጭነትና ተቀባይነት እንደሚቀነስ አስጠንቅቋል።

የትራንዚት መንገደኞች ሌላ የተሻለ አገልግሎት ማግኘት ወደሚችሉበት አገር ለመሄድ ስለሚገደዱ በቀጣይ የአገሪቱ አቪየሽን ዕድገት ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ ይኖረዋል ሲልም ያስጠነቅቃል።

አውሮፕላን ማረፊያው በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላቸው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት መመዘኛዎች አንጻር ሲታይ ጥራቱ ዝቅተኛ የሆነ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን መረጃው አመልክቷል፡፡

መረጃው ለዚህ ችግር የአጭርና የረዥም ጊዜ መፍትሔዎችንም ጠቁሟል፡፡ የአጭር ጊዜ እቅዶች ካላቸው ውስጥ አሁን ያለውን የመንገደኞች ተርሚናል በማስፋት ቢያንስ ለቀጣይ አስር ዓመታት እንዲያገለግል ማድረግ እና ዘመናዊ የክብር እንግዶች ሳሎን (VIP SALON) መገንባት የሚሉት ሲገኙበት በረዥም ጊዜ እቅድ ደግሞ አዋጪ በሆነ ቦታ አዲስ ኤርፖርት በመገንባት የቦሌ ኤርፖርትን ለቅርብ ርቀት በረራዎች እንዲሁም ልክብር እንግዶች እና ለሀገር ውስጥ አገልግሎት ማዘጋጀት የሚል የመፍትሔ ሃሳብ አስቀምጧል፡፡