አንድነት ፓርቲ የእሪታ ቀን በሚል በአዲስ አበባ የተቃውሞ ሰልፍ ሊጠራ ነው

መጋቢት ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ፓርቲው የተቃውሞ ሰልፉን የሚጠራው በዋና ከተማዋ የሚታዩትን የማህበራዊ አገልግሎቶችን ችግሮች ለመቃወም ነው።

“በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ገንዘብ የወጣባቸው መንገዶች ለምረቃ በበቁ በጥቂት ቀናት ልዩነት መፍረሳቸው፣ የከተማው ነዋሪ ለሚጠቀምባቸው የመጓጓዣ አውታሮች ተለዋጭ መንገድ ባለመዘጋጀቱ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉን፣ ትራንስፖርት ማግኘት በሁሉም አካባቢዎች አስቸጋሪ በመሆኑ የከተማይቱ የሥራ እንቃስቃሴ መዳከሙን፣ መንግሥት ‹‹የምትታለብ ላም›› በማለት የሚጠራው የኢትዮ ቴሌ ኮም አገልግሎት የለም የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱን” አንድነት በመግለጫው አትቷል።

እንዲሁም ” የከተማይቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አለመቀረፉ የከተማይቱ ኢንዱስትሪዎች ፤ንግድ ተቋማትንና ነዋሪውን እያማረረና ህይወቱን እያመሰቃቀለ ከመሄድ ውጭ ምንም አይነት ለውጥ አለማሳየቱ፡ በከተማይቱ ውሃ ማግኘት እንደ ትልቅ እድል መቆጠር በመጀመሩ ጊዜያቸውን በትምሀርት ገበታቸው ላይ በመገኘት ማሳለፍ ይገባቸው የነበሩ ተማሪዎች ውሃ ለመቅዳት ረዥም መንገድ ለመጓዝ በመገደዳቸው የትምህርት ጊዜአቸው እንዲበደል ማድረጉን” ፓርቲው አክሎ ገልጿል።

ከተማይቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ የከተማይቱ ነዋሪ ለሚገፋው አስቸጋሪ ህይወት ተጠያቂ መሆኑንና ድርጅቱ አገሪቱን የመምራት ብቃት እንደሌለውም የወቅቱ የአዲስ አበባ ሁኔታ እንደሚያሳይ ገልጿል።የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የአዲስ አበባ ምክር ቤት  ‹‹የእሪታ ቀን›› በሚል ስያሜ በ1ወር ጊዜ ውስጥ ሠላማዊ ሠልፍ ለማድረግ መወሰኑን አስታውቋል።

የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች ሰላማዊ ሰልፉ በሚደረግበት ቀን በነቂስ በመውጣት በስርዓቱ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ለመግለፅ እንዲዘጋጁም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።
ኢትዮጵያውያን በመብራት፣ በውሃ፣ በኑሮ ውድነት፣ በስልክና ሌሎች ማህበራዊ ችግሮች እየተቸገሩ መሆናቸውን በተደጋገሚ ይገልጻሉ። መንግስት አገሪቱ 11 በመቶ እንዳደገች በተደጋገሚ ይገልጻል።