ኅዳር ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የገዥው መንግስት በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ የብአዴን አባላትን በየክፍለ ከተማው ሰብስቦ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዙሪያና በተከሰቱት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ዙሪያ ሰሞኑን ባነጋገረበት ጊዜ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰበብ የታሰሩት ነጋዴዎችን ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ አባላቱ ጠይቀዋል።
ጥያቄውን ያቀረቡት የብአዴን አባላት እንደተናገሩት የታሰሩት ነጋዴዎች በአጋጣሚ የንግድ ድርጅታቸውን ከፈተው አገልግሎት ሲሰጡ የተገኙት ብቻ መሆናቸውን ገልጸው ፤በከተማዋ በሰላማዊው የስራ ማቆም እድማ የተሳተፈው ሁሉም የከተማዋ ነጋዴዎች ቢሆኑም፣ ከቀበሌ አመራሮች ጋር ባላቸው የተበላሸ ግንኙነት በቂም በቀል ነውና ይፈቱ ሲሉ ጠይቀዋል። አባላቱ በውይይቱ ‹‹ የተቃውሞው መነሻ ምንድን ነው?›› በማለት ከከፍተኛ አመራሩ ለተጠየቁት ጥያቄ ባስቀመጡት ምላሽ፣ ከሃያ አምስት አመት በፊት የተጠየቀው የወልቃይት ማንነት ጥያቄ በወቅቱ በተገቢው መንገድ አለመመለሱ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተዳምሮ ህብረተሰቡ የስርዓት ለውጥ እንዲመጣ የጠየቀበት ሁኔታ መከሰቱን ተናግረዋል፡፡
ተሰብሳቢ የብአዴን አባላቱ እንደተናገሩት ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ ለወጣቶች ስራ ፈጠራ በሚል ቢመደብም ፣ የገዥው መንግስት አመራሮች ግን ገንዘቡን ላልተገባ አገልግሎት በማዋል ፣ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው መጠቀሚያ ማድረጋቸው ሌላው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሃገሪቱ ላይ ያለው ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖር አብዛኛውን ህብረተሰብ ለከፋ ድህንት ማጋለጡን ገልጸው በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ የአንድ ብሄር የበላይነት የገነነበት ስርአት እስካልተወገደ ድረስ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሩ እንደሚቀጥል ያላቸውን ስጋት በድፍረት ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡
ከብአዴን የህዋስ አባላት ጋር የሚደረገው ውይይት አሁንም የቀጠለ ሲሆን አባላቱ ህብረተሰቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመፍራት ለስርዓቱ ታማኝ እንዲሆን ቅስቀሳቸውን እስከ ታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ለማሳመን ጥረታቸውን እንዲቀጥሉ አደራ ተጠሎባቸዋል፡፡