(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2010)
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ከጥር 12/2010 ጀምሮ ለ8 ቀናት በባህርዳር ከተማ እንደሚካሄድ የኢሳት ምንጮች ገለጹ።
በስብሰባው ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ከአራት ጊዜ በላይ በጉባኤው ተመርጠው የሰሩ የብአዴን አባላት ይገኛሉ ተብሏል።
ሕወሃትም ከጉባኤው በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ አመራሮች የሚገኙበት ድርጅታዊ ጉባኤ ከጥር 3/2010 ጀምሮ ለ8 ቀናት በመቀሌ እንደሚያካሂድ ታውቋል።
ኢሳት ከምንጮች ያገኘው ሰነድ እንደሚያመለክተው የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የመወያያ አጀንዳዎች 4 ናቸው።
የጥልቅ ተሃድሶ አፈጻጸምን በመገምገም የቀጣይ ትኩረት ነጥቦች ላይ መወያየት አንዱ ነው።
የወረዳና የቀበሌ ምክር ቤት ምርጫ እቅድና የ12ኛው የብአዴን ድርጅታዊ ጉባኤ ዝግጅት ላይ መወያየትም ተጨማሪ አጀንዳዎች ናቸው።
ሌሎች ጉዳዮች ተብለው በሚስጥር የተያዙ አጀንዳዎች እንዳሉም ከምንጮች ያገኘንው መረጃ ያመለክታል።
የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከጥር 12/2010 ጀምሮ በባህርዳር ከተማ ለ8 ቀናት እንደሚካሄድም ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ሕወሃት ከቀጣዩ ጉባኤ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ የከፍተኛ አመራሮች ድርጅታዊ ጉባኤ በመቀሌ ከተማ እንደሚካሄድ መግለጹ ይታወሳል።
በዚሁ ጉባኤ ላይ ከ2 ሺ 500 በላይ ተሳታፊዎች ሲገኙ አጀንዳውም በግምገማ ስራ አስፈጻሚው የወሰናቸው ጉዳዮች በካድሬው ተቀባይነት እንዲያገኝ ማድረግን ያለመ መሆኑ ነው የተነገረው።
በጉባኤው የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች እንደሚገኙም ተገልጿል።
ሕወሃት 35 ቀናት ከቆየበት ግምገማ በተጨማሪ ሌላ ግምገማ በከፍተኛ ካድሬዎች ለማድረግ መወሰኑ አሁንም ገና ያልቋጫቸው ጉዳዮች እንዳሉት ያሳያል ነው የተባለው።
ከምንጮች ያገኘንው መረጃ እንደሚያመለክተው በእስረኞች አፈታት ውሳኔ ላይ ሕወሃት አሁንም ያልተስማማባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ይነገራል።
በተለይም ከአማራ ክልል ከወልቃይት ጋር በተያያዘ ታፍነው ወደ ትግራይ የተወሰዱ 4መቶ የሚጠጉ ሰዎች እንዲለቀቁ ብአዴን ያቀረበው ጥሪ ተቀባይነት አለማግኘቱ ታውቋል።
በሕገወጥ መንገድ ከአማራ ክልል እየታፈኑ የተወሰዱት ሰዎች በትግራይ ባዶ 6 ጭለማ ቤቶች እንዳሉ ይነገራል።