ሁለት የስውዲን ፓርላማ አባላት ለመንግስታቸው ጥሪ አቀረቡ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2010)

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ግድያና የሰብአዊ መብት ጥሰት ችላ ከማንልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ሲሉ ሁለት የስውዲን ፓርላማ አባላት ለመንግስታቸው ጥሪ አቀረቡ።

አንድሬስ አስተርበርግና ማሪያ አንደርሰን የተባሉ የስዊዲን ፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን ጭፍጨፋ በቸልታ የምናየው ከሆነ አጠቃላይ የእርስ በርስ ጦርነት ሊከሰት ይችላል ሲሉ አስተጠንቅቀዋል።

የስውዲን መንግስትም አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ በሚል ጥያቄ ያቀረቡት አባላቱ ከዚህ በኋላ ከኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ባዶ ተስፋ ጋር የምንተባበርበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።

ሁለት የስዊዲን የፓርላማ አባላት ያቀረቡት ጥያቄ በሀገሪቱ ቴሌቪዥን የተላለፈው ዛሬ ነው።

ለፓርላማው የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በቀጥታ እንዲሁም ለስዊዲን መንግስት በተዘዋዋሪ ባስተላለፉት ጥሪ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለፖለቲካ ፍጆታ በሚል በቸልታ ከማናልፍበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ብለዋል።

ባለፈው ታህሳስ ወር ብቻ በሀገሪቱ የተፈጸሙትን ግጭቶችና ግድያዎች ብንወስድ የኢትዮጵያ ሁኔታ ወደ አደገኛ አቅጣጫ እያመራ መሆኑን እንረዳለን ሲሉ ገልጸዋል የፓርላማ አባላቱ።

ለዚህም የገዢው ፓርቲ ባለስልጣን ንግግርን በምክንያትነት ይጠቅሳሉ።

የቀድሞ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ አማራና ኦሮሞ እሳትና ጭድ ናቸው ብለው በአደባባይ የተናገሩት በሀገሪቱ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሁለቱ ብሔረሰቦች መካከል ደም ለማፋሰስ መንግስት እቅድ እንዳለው የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው ገዢ ፓርቲ ያለምንም ተጠያቂነትና ሃላፊነት የውጭው አለም አብሮ መስራቱን የሚቀጥል ከሆነ የእርስ በርስ ጦርነት በሀገሪቱ መፈንዳቱ የማይቀር ነው ሲሉ አንድሬስና ማሪያ አስጠንቅቀዋል።

የስዊዲን መንግስት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጣቸው የጠየቁት ሁለቱ የፓርላማ አባላት ከእንግዲህ ከዚህ መንግስት ጋር የሚደረገው ማንኛውም ግንኙነት እንዲፈተሽ ጥሪ አድርገዋል።

የስዊዲን መንግስት በኢትዮጵያ ምን እየተደረገ እንደሆነ ገዢውን ፓርቲ እንዲጠይቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ላለው ጭፍጨፋ ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ ጫና እንዲፈጥር የፓርላማ አባላቱ ጠይቀዋል።

ገዢው ፓርቲ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች እፈታለሁ ማለቱን የጠቀሱት የፓርላማ አባላቱ በባዶ ተስፋ አብረን የምንዘልቅበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።

አሜሪካ እንኳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ፖሊሲ ለመለወጥ እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ወቅት የስዊድን መንግስት ጉዳዩን በቸልታ ሊመለከተው አይገባም ሲሉ ጉዳዩን በአጽንኦት ገልጸዋል።

ስዊድን በአፋጣኝ የገዢው ፓርቲ የጭፍጨፋ ድርጊትን እንድታወግዝና ህጋዊ ምርመራ እንዲደረግ ግፊት እንድታደርግም ጠይቀዋል።