በአማራ ክልል ከ20 በላይ ሰዎች ተገድለዋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 30/2010)

በአማራ ክልል ተደጋጋሚና ድንገተኛ ጥቃት ባለፈው ወር ብቻ በአገዛዙና በመንግስት ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በብሔራዊ የጸጥታና ደህንነት ምክር ቤት ላይ የቀረበ ሪፖርት አመለከተ።

ከሟቾቹ መካከል የቀበሌና የወረዳ አስተዳደር ባልደረቦች እንደሚገኙበት ከአማራ ክልል ለምክር ቤቱ የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል።

የብሔራዊ፣ የጸጥታና ደህንነት ምክር ቤት ከዚህ በፊት የወጣውን እቅድ እንደገና በመከለስ አዲስ የጋራ ዘመቻ ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ገልጸዋል።

በብሔራዊ የጸጥታና ደህንነት ምክር ቤት በሀገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ቀውስ ባለመረጋጋቱ ከፌደራልና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል።

እናም በዚሁ ስብሰባ የተሳተፉት የምክር ቤቱ አባላትና የጸጥታ ሃይሎች በሀገሪቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ካልተፈለገ በሃይል ለመቀልበስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያምና የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ በመሩት የምክር ቤቱ ስብሰባ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑ ነው የተገለጸው።

በኦሮሚያ በክልሉ ፖሊስ አባላትና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ተደጋጋሚ ግጭት ተከስቶ በርካቶች ተገድለዋል።

በጋራ መስራት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናልም ብለዋል ሪፖርት አቅራቢዎቹ።

በተለይ ቄሮ የተባለው የኦሮሞ ወጣቶች አደረጃጀትን መመከት ተስኖናል ነው ያሉት።

በአማራ ክልልም በመንግስት ታጣቂዎችና የስራ ሃላፊዎች ላይ ባልታወቁ አካላት ጥቃት እንደሚሰነዘር ተገልጿል።

ከአማራ ክልል ተሳታፊዎች የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው ባለፉት ወራት ብቻ ከሃያ የሚበልጡ የቀበሌና የወረዳ አስተዳደር ባልደረቦች መገደላቸው ነው የተነገረው።

ከመቀሌና ከጎንደር የሚነሱ የሰላም ባስ የሕዝብ ማመላለሻና ሌሎች የጭነት ተሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ መጠቃታቸውም በሪፖርቱ ቀርቧል።

ማናቸውንም ስፖርታዊና ሕዝባዊ ክንውኖች ከአጎራባች ክልሎች ጋር ማድረግ ባለመቻሉም ዝግጅቶች መሰረዛቸውን የአማራ ክልል ሪፖርት አመልክቷል።

እናም በኢትዮጵያ ያለውን ቀውስ ለመፍታት ሃይል ሳይሆን ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ የጸጥታ አካላት ሪፖርት ማቅረባቸውን ከልዩ ልዩ ምንጮች ያገኘንው መራጃ ያመለክታል።