የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ የአገሪቱ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አሳሰበ

ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2009)

በኢትዮጵያ ጉብኘትን እያደረጉ ያሉት የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በሃገሪቱ ቆይታቸው የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጉዳይ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ የብሪታኒያ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አሳሰበ።

ሪፕሪቭ የተሰኘውና የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጉዳይ የሚከታተለው ድርጅቱ, ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ባለፈው አመት ስልጣን በተረከቡ ጊዜ ለሃገሪቱ ዜጎች መብት መከበር የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ የቦሪስ ጆንሰንን የኢትዮጵያ ጉብኝት አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ዩጋንዳንና ኬንያ የሚጎበኙ የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ሃገራቸው ከሶስቱ ሃገራት ጋር ባላት ዘርረ-ብዙ ግንኙነት ዙሪያ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሃሙስ በአዲስ አበባ ጉብኝታቸውን ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በሃገሪቱ ቆይታቸው የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይን ችላ ማለት እንደሌለባቸውና ብሪታንያ ለዜጋዋ መብት መከበር ማድረግ ያለባትን ሁኔታ በግልፅ እንዲያሳውቁ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ (ሪፕሪቭ) ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።

“የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ይህንኑ ሳይደርጉ ከቀሩ፣ ብሪታኒያ ዜጋዋ በውጭ ሃገር መብቱ ሲጣስ ያለ ምንም አፀፋ ዝም ብላ ለመመልከት ፈቃደኝነቷን የሚያሳይ ነው” ሲሉ  የሰብዓዊ መብት ተቋሙ ዳይሬክተር ማያ ፎ’አ ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ቦሪስ ጆንሰን ከኢትዮጵያ ውጭ ጉግዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ሃሙስ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን፣ በዚሁ ውይይት የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይ መነሳቱ እንደማይቀር ተነግሯል። ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ የብሪታኒያ የልዑካን አባላት እስካሁን ድረስ የሰጡት መረጃ የለም።

ባለፈው ወር 53 የሚሆኑ የብሪታኒያ የፓርላማ አባላት ለሃገራቸው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ ደብዳቤን በመጻፍ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የሚለቀቁበት ሁኔታ ላይ ተጨባጭ ጥረት እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።

የፓርላማ አባላቱ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት አቶ አንዳርጋቸው ህጋዊ የምከር አገልግሎት እንዲያገኙ የገቡትን ቃል እንዳላከበሩና ብሪታኒያ ሁኔታውን በዝምታ መመልከት እንደሌለባት አሳሰበዋል። ከተለያዩ አካላት ሲቀርብ የነበረውን ይህንኑ ጥያቄ ተከትሎ የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወደ ኢትዮጵያ ማቅናታቸው ተነግሯል።