የባለስልጣናት ጥቅማጥቅሞች ዝርዝር

ጥር ፲ ( አሥር )ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከስልጣን የሚለቁ የገዢው ፓርቲ ሹመኖች ቀድሞ ያገኙት ስለነበረው ጥቅም

በፊት የነበረው አዋጅ መሻሻሉን በተመለከተ ትናንት በዜና ዝግጅታችን ማቅረባችን ይታወሳል። አዋጁን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎች ደርሰውናል

ገዢው ፓርቲ ከስልጣን የሚሰናበቱ ባለስልጣናትን ጥቅማጥቅሞች ለማስከበር ቀደም ብሎ አዋጅ ቁጥር 653/2001ን አውጥቶ ላለፉት 7 ዓመታት ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። ይሁን እንጅ አዋጅ ለማሻሻል በሚል  ጥር 9፣ 2009 ዓም ሌላ  ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማው ቀርቧል፡፡ ረቂቁን አዋጅ ለማውጣት ያስፈለገው እነዚህ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና የሕዝብ ተመራጮች በተለያዩ ምክንያቶች ከቦታቸው ሲነሱ የሚጠበቅላቸውን መብቶኛና ጥቅማ ጥቅሞች በዝርዝር ባለመስፈራቸው መሆኑን አዋጁ ይጠቅሳል።

አዋጅ ቁጥር 653/2001 ለመብቶችና ጥቅሞች አሰጣጥ የሥራ አስፈጻሚውን ለሁለት ምድብ የሚከፈል ነው፡፡ የመጀመሪያው ምድብ የሀገርና የመንግስት መሪዎች ንዑስ ምድብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ምድብ ነው፡፡ በአዋጁ ውስጥ ለሀገርና ለመንግስት መሪዎች የተጠበቁ መብቶችና ጥቅሞች በአንጻራዊነት ሲታዩ ለከፍተኛ የመንግስት ባልሥልጣናት ከተጠበቁት መብቶችና ጥቅሞች የተሻሉ በመሆናቸው በዚህ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ አለመካተታቸውን አዋጁ ይጠቅሳል።

በከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ምድብ ሥር የተካተቱት ሚኒስትሮችና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና  የፓርላማ አባላት ናቸው። የመጀመሪያው የባለስልጣናቱ ጥቅም የመቋቋሚያ አበል የሚባለው ሲሆን ቀድሞ ባለስልጣናቱ በመቋቋሚያ አበልነት ይሰጣቸው የነበረው እስከ 18 ወራት የሚደርስ ክፍያ አሁን ወደ 24 ከፍ ብሎአል።

ይህ ማሻሻያ ከኃላፊነት ለተነሱ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና ከኃላፊነት ለተነሱ የምክር ቤት አባላት ሁሉም እንዲሆን ታሳቢ መደረጉ በአዋጅ ተደንግጓል። በዚህ ስሌት መሰረት አንድ አንድ ሚኒስትር ወይም ከዚያ በታች የሆነና አዋጁ የሚመለከተው ሹም ለመቋቋሚያ አበል እስከ 120 ሺ ብር ያገኛል።

ሌላው ክፍያ ደግሞ የስንበት ክፍያ የሚባለው ሲሆን፣ አንድ አመት ያገለገለ ባለስልጣን የ6 ወር ደሞዙ እና ለእያንዳንዱ አመት አገልግሎቱ ደግሞ የመጨረሻውን ወር ደሞዙን ግማሽ እየተሰላ ይከፈለዋል። በዚህ መሰረት አንድ 5 ሺ ብር የሚከፈለው እና 10 አመታት ያገለገለ ባለስልጣን እስከ 55 ሺ ብር የስንብት ክፍያ ያገኛል። ሌላው ጥቅም ደግሞ የመኖሪያ ቤትን የተመለከተ ሲሆን አንድ የምርጫ ዘመን እና ከዚያ በታች ለተሰጠ አገልግሎት፣

ሚኒስትር ከሆነ መነሻው የዘጠኝ ወራት ሙሉ ክፍያ ሆኖ ከአንድ የምርጫ ዘመን በላይ ላለው ለእያንዳንዱ ተጨማሪ የአንድ ዓመት አገለግሎት የአንድ ወር ክፍያ አንድ ሁለተኛ እየታከለ እንዲሰላ፤ ሚኒስትር ዴኤታ ከሆነ መነሻው የስድስት ወራት ሙሉ ክፍያ ሆኖ ከአንድ የምርጫ ዘመን በላይ ለለው ለእያንዳንዱ ተጨማሪ የአንድ ዓመት አገልግሎት የአንድ ወር ክፍያ አንድ ሁለተኛ እየታከለ እንዲሰላ፤

ምክትል ሚኒስትር ከሆነ መነሻው የአራት ወራት ሙሉ ክፍያ ሆኖ ከአንድ የምርጫ ዘመን በላይ ላለው ለእያንዳንዱ ተጨማሪ የአንድ ዓመት አገልግሎት የአንድ ወር ክፍያ አንድ ሁለተኛ እየታከለ እንዲሰላ፤ እንዲሁም ማንኛውም ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ቢያንስ ሁለት የምርጫ ዘመን አገልግሎት ከኃላፊት ከተነሳ ወይም፣ አንድ የምርጫ ዘመን እና ከግማሽ ያላነሰ አገልግሎት በሕመም፣ በአካል ጉዳት ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ሌላ ምክንያት ከኃላፊነት ከተነሳ፣ ለራሱና ለቤተሰቡ መኖሪያነት የሚያገለግል ራሱ ኪራይ እየከፈለ የሚገለገልበት የመኖሪያ ቤት እንዲሰጥ ይፈቅዳል፡፡ የመኖሪያ ቤቱ ደረጃም ሚኒስትር ሲሆን ሦስት መኝታ ክፍሎች ያሉት፤ ሚኒስትር ዴኤታ ወይም ምክትል ሚኒስትር ሲሆን ሁለት መኝታ ክፍሎች ያሉት እንዲሆን ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡

ይህ ጥቅም፣ ከኃላፊነት ለተነሳ ሚኒስትር፣ አፈጉባኤ፣ የመንግሥት ተጠሪና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በእኩል ደረጃ፣ ከኃላፊነት ለተነሳ ሚኒስትር ኤዴታ፣ ምክትል አፈጉባኤ፣ ምክትል የመንግሥት ተጠሪና ምክትል የተቃወሚ ፓርቲ ተጠሪ በእኩል ደረጃ፣ ከኃላፊነት ለተነሳ ምክትል ሚኒስትር፣ ረዳት የመንግሥት ተጠሪ እና ለተቃዋሚ ፓርቲ ረዳት በእኩል ደረጃ ተፈጻሚ እንደሚሆን በአዋጁ ተደንግጓል። በዚህ መሰረት አንድ 10 አመታትን ያገለገለ 5 ሺ ብር የወር ደሞዝ የሚያገኝ ባለስልጣን ከሚሰጠው መኖሪያ ቤት በተጨማሪ እስከ 105 ሺ ብር የሚደርስ ክፍያም ያገኛል።

በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው ደግሞ የተሽካርካሪ ጥቅም ሲሆን፣ ተሽከርካሪን በተመለከተ ነባሩ አዋጅ ለሀገር መሪና ለመንግሥት መሪ እንዲሁም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት እስከ ሁለት የሚደርሱ የመንግስት ተሽከርካሪዎችን የሚፈቅድ ሲሆን፤ በቀረበው ማሻሻያ አንድ የምርጫ ዘመን አገልግሎት ከኃላፊነት ለተነሳ ወይም አንድ የምርጫ ዘመን እና ከግማሽ ያላነሰ አገልግሎት በሕመም፣ በአካል ጉዳት ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ሌላ ምክንያት ከኃላፊነት ለተነሳ ከፍተኛ የመንግሠት ኃላፊ እና የምክር ቤት አባል የሚከፈለውን የአበል ክፍያ መጠን ለክፍያ መነሻ የሆነውን ወር መጠን ከፍ በማድረግ አበሉ ከፍ እንዲል እና እንዲጨምር ተደርጓል፡፡

ሌላው ማንኛውም ማኒስትር የሆነ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ ቢያንስ ሁለት የምርጫ ዘመን አገልግሎ ከኃላፊነት ከተነሳ ወይም፣ አንድ የምርጫ ዘመን ከግማሽ ያላነሰ አገልግሎ በሕመም፣ በአካል ጉዳት ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ሌላ መክንያት ከኃላፊነት ከተነሳ፣ አንድ የቤት አውቶሞቢል በመንግሥት እንዲመደብለት ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረት ለሚመደበው የቤት አውቶሞቢል የሾፌር ደመወዝ፣ የነዳጅ፣ የጥገና እንዲሁም ሌላ ወጪ በመንግሥት ይሸፈናል፡፡

አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በስልጣን ላይ በሚቆይበት ጊዜ 500 ካሬ ሜ የቤት መስሪያ ቦታ ያገኛል። በተለያዩ ስብሰባዎች እና የፊልድ አበሎች እንዲሁም  በስልጣን ላይ በሚቆይበት ጊዜ የሚያገኛቸው ጥቅማጥቅሞች ሲታሰቡ፣ የመንግስት ስልጣን ወደ ሃብት የሚወስድ አቋራጭ መንገድ መሆኑን መታዘብ ይቻላል።

ኢትዮጵያ ከ35 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ እዳ አለባት። በዚህ አመት ብቻ 5 ሚሊዮን 600 ሺ ሰዎች አስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ከ7 ሚሊዮን ያላነሱ ዜጎች ደግሞ በምግብ ለስራ በሚል ፕሮግራም አሁንም በድጋፍ ይኖራሉ። በአገሪቱ የሚታየው የኑሮ ውድነት እጅግ ለሚበዛው ህዝብ ከፍተኛ ፈተና ደቅኖበታል።