(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 23/2011)ባለፈው ቅዳሜ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የፊታችን ዕሁድ የቀብር ስነስርዓታቸው እንደሚፈጸም ተገለጸ።
አስክሬናቸው ቅዳሜ ሚያዚያ 26 ከጀርመን ወደ አዲስ አበባ እንደሚገባም መንግስት አስታውቋል።
በብሔራዊ ደረጃ የሚፈጸመው የቀብር ስነስርዓት ኮሚቴ ተቋቁሞ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑም ታውቋል።
በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ በዶክተር ኢዮብ ተካልኝና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የሚመራው የቀብር አስፈጻሚ ኮሚቴ መግለጫ የሰጠ ሲሆን ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እሁድ ሚያዚያ 27 ከቀኑ 9 ሰዓት በጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተክርስቲያን ግብዓተ መሬታቸው እንደሚፈጸም አስታውቋል።
በጀርመን ፍርንክፈርት በነገው ዕለት የዶክተር ነጋሶ የአስክሬን ሽኝት እንደሚደረግም በፍርራንክፈርት የሚገመው ቆንስላ ጄነራል ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
ጽሕፈት ቤቱ በጀርመን ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ዶክተር ነጋሶን እንዲሰናበት ጥሪ ማድረጉም ታውቋል።
ለስድስት ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ነጋሴ ጊዳዳ በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ያለፈው በ76 ዓመታቸው መሆኑን ከህየወት ታሪካቸው ለመረዳት ተችሏል።