የቀድሞው የኢቴቪ ጋዜጠኛ ሰለሞን መንግስቴ ተናገረ

ጥቅምት ፲፫ (አስራ ሶስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውስጥ የሚዲያ ነጻነት አስከፊ ደረጃ ላይ በመድረሱ በወር ሶስት አራት ጋዜጠኞ ስራቸውን እንደሚለቁ፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእንግሊዘኛው ፕሮግራም ባልደረባ ሰለሞን መንግስቴ ለኢሳት ገለጸ።

ጋዜጠኛ ሰለሞን መንግስቴ ለኢሳት እንደገለጸው፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬድዮ ጋዜጠኞች፤ እንጀራ ሆኖባቸው በምርጫ ማጣት ይስሩ እንጂ፤ ምንም አይነት የጋዜጠኝነትም ይሁን የኤዲቶሪያል ነጻነት እንደሌላቸው ገልጿል።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተቋቋመበት ሕግ የኤዲቶሪአል ነጻነት እንዳለን ቢናገርም የመንግስት ባለስልጣናት የበላይ አካላት የኢህአዴግ አባላት እንድንሆን በማስገደድ፤ ፈጽሞ የማናውቀውን ጽሁፍ በማውጣት አንብቡ በማለትና የፕሮፓጋንዳ ስራዎችን እንድንሰራ በማስገደድ፤ የጋዜጠኝነት ነጻነታችንን አሳጥተውናል ብሏል።

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውስጥ በእንግሊዘኛው ቋንቋ ፕሮግራም በዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ሪፖርተርና ዜና አንባቢ በመሆን ለ3 አመታት ያገለገለው ሰለሞን መንግስቴ፤ በኢቲቪ ውስጥ ባለው የነጻነት እጦት የተነሳ፤ በየወሩ ሶስት አራት ጋዜጠኞች ስራ እንደሚለቁም ተናግሯል።

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውስጥ ለመቀጠር የገዢው ፓርቲ አባል መሆን ወይንም ታማኝ አገልግሎት መሆን እንደቅድመ ሁኔታ ይቀመጣል ያለው ሰለሞን መንግስቴ፤ ልክ በየወሩ እንደሚለቁት ሶስት አራት ጋዜጠኞች፤ እሱም በቃኝ ብሎ አንገፍግፎት እንደለቀቀ ተናግሯል።

ሰለሞን መንግስቴ በአሁኑ ሰዓት በስደት ይገኛል።