የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አባል ስንታየሁ ቸኮል በእስር ቤት ውስጥ ችግር እየደረሰበት መሆኑን ተናገረ

ጥቅምት ፲ (አሥር) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- ከሕግ አግባብ ውጪ ታስሮ በእስር ላይ የሚንገላታው የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አባል ስንታየሁ ቸኮል በእስር ቤት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙበት ለፍርድ ቤቱ በዝርዝር ተናግሯል።

የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማእከላዊ በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ በፌስታል እንዲፀዳዳ መደረጉን፣ ድብደባ እንደደረሰበት፣ በሃያ ስምንት ቀናት ቆይታው ለአንድ ቀን ብቻ እንዲናፈስ መደረጉን እና በጨለማ ክፍል ውስጥ ታስሮ ሰቆቃ እንደተፈጸመበት ለአራዳ ፍርድ ቤት የደረሰበትን የመብት ጥሰቶች በዝርዝር አስረድቷል። ስንታየሁ ቸኮል ያቀረበውን አቤቱታ መርማሪ ፖሊስ ማስተባበያ ሰጥቷል።

አቃቤሕግ ምርመራውን ለመጨረስ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠኝ ባለው መሰረት  ፍርድ ቤቱ ለህዳር 8 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል። ስንታየሁ ቸኮል ከአይኑና እግሩ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የጤና ችግር አጋጥሞታል። በደፍረቱና በጠንካራ አቋሙ የሚታወቀው ስንታየው ከዚህ ቀድም በተደጋጋሚ እየታሰረ ተፈትቷል።