ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አመታት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከሚገቡ ግንባር ቀደም አገራት ደረጃ ተመደበች

ጥቅምት ፲ (አሥር) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በዓለማችን ውስጥ በፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ለቀጣይ እንደ አገር ለመቀጠል ከሚያሰጋቸው አገራት ውስጥ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያ አንዷ ናት ሲል የአሜሪካ የጥናት ማእከል አስታውቋል።

እያደገ ከመጣው የሕዝብ ብዛት እድገት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ እድገት የሌላት ድሃዋ አገር ኢትዮጵያ፣ ፍትሃዊ የሆነ አስተዳር ያልሰፈነባት አፋኝ ስርዓት ያላት መሆኑን ጥናታዊ ሪፖርቱ አመልክቷል። ይህን ጭቆና ተከትሎ በዓለማችን ከፍተኛ አደጋ ካንዣበባቸው ማልዳይቪስ፣ ሞሪታኒያ፣ አልጀሪያ በመቀጠል ኢትዮጵያ በ4ኛ ደረጃ ተቀምጣለች። በግብርና ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ምጣኔሃብታዊ እድገት ድርቁን ተከትሎ ከፍተኛ ተግዳሮቶች ገጥመዋታል። በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኘው የኢንዱስትሪው መስክ ከሌላው ዓለም ጋር በነጻ ገበያ የመፎካከር አቅሙ ደካማ ነው ሲል ሪፖርቱ ይዳስሳል።

በእርስበርስ ጦርነት ስትታመስ የቆየችው ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት በኋላ አገሪቱን የተቆጣጠሩት በአናሳዎች የሚወከሉት የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ህወሃት ሌሎች የአገርቱን ታላላቅ ብሄረሰቦች ያገለለ አስተዳደር መመስረታቸው ለአገርቷ መጻኢ እጣፋንታ አጣብቂኝ ውስጥ መግባት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል ይላል ጥናቱ።

ናይጀሪያ፣ ቱርክ፣ ሩሲያ፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ጆርዳን እና ቻይና በቅደምተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ደረጃን ይዘዋል። በደረጃ ሰንጠረዡ መሰረት አብዛሃኞቹ ሰላምና መረጋጋት የተሳናቸው አገራት የአፍሪካ እና መሃከለኛው ምስራቅ አገራት መሆናቸውን አሜሪካን ኢንተርፕራይዝ ኢንስቲትዊት /American Enterprise Institute/ በጥናታዊ ሪፖርቱ ዘግቧል።