የቀድሞው የአንድነት አመራር ለ3ኛ ጊዜ የዋስትና ገንዘብ አቅረበ

ሰኔ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው አቶ ዳዊት አስራደ ሰኔ 3/2007 ዓ.ም አራዳ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ በ5 ሺ ብር ዋስ እንዲፈታ ዋስትና የተፈቀደለት ቢሆንም ገንዘቡን ካስያዘ
በኋላ ዋስትናው እንደተነሳ ተነግሮት በእስር ላይ እንዲቆይ ተደርጓል።
ፖሊስ አቶ ዳዊትና ሌሎች ተከሳሾች ምስክሮችን ያባብሉብኛል በሚል ለ14 ቀን ታስረው እንዲቆዩ ቀጠሮ ጠይቆ የነበር ቢሆን ፍርድ ቤቱ ግን አቶ ዳዊት አስራደ፣ አቶ አለነ ማህፀንቱና ወይዘሪት ሜሮን አለማየሁ የ5000 ብር ደሞዝ ያለው
የሰው ዋስ ወይንም ገንዘብ አስይዘው ከእስር እንዲወጡ ወስኗል።
የአቶ ዳዊት አስራደ ቤተሰቦች መፍቻ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያ ሲሄዱ አቶ ዳዊት ለቄራ ፖሊስ ጣቢያ ተላልፈው መሰጠታቸውን ጠበቃውን ዋቢ በማድረግ ጋዜጣው ዘግቧል።
መንግስት አይ ኤስ አይ ኤስን ለመቃወም በጠራው ሰልፍ ሰበብ የታሰረው አቶ ዳዊት አስራደ በተመሳሳይ ክስ ለሶስተኛ ጊዜ የዋስትና ገንዘብ እያስያዘ እንደገና በእስር ላይ የቆየ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ 25 ሺህ፣ በቀጣይ 6 ሺህ፣ እንዲሁም
በትናንትናው ዕለት 5 ሺህ ብር በአጠቃላይ 36 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ እንደገና ታስሯል።
አቶ ዳዊት አስራደና ወይዘሪት ሜሮን አለማየሁ ሚያዝያ 14 መንግስት ላይ በተነሳው ተቃውሞ ሰበብ በአንድ ጉዳይ ሁለት ክስ ተመስርቶባቸው በሁለት ፍርድ ቤቶች ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል። በቄራና ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያም በፈረቃ
ሲታሰሩ ቆይተዋል።