ሚያዚያ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የትንሳዔ በዓል ገበያ በአዲስ አበባ የተረጋጋ ቢመስልም አሁንም የሸቀጦች ዋጋ በተለይ ከዝቅተኛው ኀብረተሰብ አቅም በላይ መሆኑን በሾላ እና በሳሪስ ገበያ ትላንትና ያሰባሰብናቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የጤፍ ዋጋ ማኛ ከ1850-2000ብር በኩንታል፣ነጭ ጤፍ ከ1750-1800፣ሰርገኛ ከ1600-1700 ዋጋ ይጠየቅበታል፡፡ ቅቤ እንደረጃው ከ180-195 ብር በኪሎ በተለይም ለጋ ቅቤ የሸኖ በኪሎ እስከ 200 ብር ፣ ዶሮ የአበሻ ከ130-170 ብር፣ የፈረንጅ ዶሮ ከ120-140፣ የአንድ ዕንቁላል የአበሻ ከ2 ብር ከ 40- 2 ብር ከ 50፣ አንድ የፈረንጅ ዕንቁላል ከ 2 ብር 25 እስከ 2 ብር 35 ይሸጣል፡፡ የአበሻ ቀይ ሸንኩርት ከወትሮው ከፍ ብሎ ከ13 ብር እስከ 15ብር በኪሎ እየተሸጠ ሲሆን የፈረንጅ ሸንኩርት በኪሎ ከ7 እስከ 8 ብር፣ ነጭ ሸንኩርት ከ30 እስከ 35 ብር በኪሎግራም ይሸጣል፡፡ነጭ ሸንኩርት ከሌላው ዓውደዓመት የቀነሰ መስሎ ቢታይም አሁንም ዋጋው የሚቀመስ አለመሆኑን ያነጋገርናቸው ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ለዶሮ ማጠቢያ ብዙ ሰዎች የሚጠቀሙበት ሎሚ በኪሎ ከ22 እስከ 25 ብር፣ቃሪያ ደግሞ በኪሎ ከ20 እስከ 22 ብር በመሸጥ ላይ ነው፡፡
የአነስተኛ በግ ዋጋ እስከ ብር 1200 ብር የሚጠራ ሲሆን ከብር 850 እስከ 1000 ብር እየተሸጠ ነው፡፡መካከለኛ በግ ከብር 1400-1800 ፣ሙክት በግ ከብር 2 ሺ 300-3 ሺ ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡
በተለይ ፒያሳ በሚገኘው አትክልት ተራ መንግስት የሸቀጦች የዋጋ ተመን በማውጣት ከዚያ በላይ ነጋዴዎች እንዳይሸጡ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ ሲሆን ይህ በሸቀጦች ዋጋ ላይ ምን ሊያስከትል እንደሚችል እስካሁን የታወቀ ነገር የለም፡፡ነገር ግን ከዚህ ቀደም የአዲስአበባ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በወሰደው ተመሳሳይ እርምጃ ምክንያት ነጋዴዎች ሸቀጦቻቸውን ለመሸጥ ፍላጎት ማጣት ጋር ተያይዞ እጥረት በመፈጠሩ እንደሸንኩርት ያሉ ሸቀጦች ዋጋቸው መሰቀሉ የሚታወስ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የአመት በአል ገበያን ተከትሎ ትራፊክ ፖሊሶች እየዘረፉን ነው በማለት ሾፌሮች ምሬታቸውን ገልጸዋል። ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ሾፌሮች ለኢሳት እንደገለጹት ትራፊክ ፖሊሶች ምሽት አካባቢ በብዛት በመውጣት ከአሽከርካሪዎች ገንዘብ ይቀበላሉ። ሰሞኑን በተለይ ከሀረር ወደ አዲስ አበባ ባለው መስመር ትራፊክ ፖሊሶች በብዛት በመውጣት ከሾፌሮች ጋር ግብ ግብ እስከ መግጠም ደርሰዋል።