አንድነት ፓርቲ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ጠየቀ

ሚያዚያ ፳፮ (ሃያ ስድስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ሚያዚያ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ይግባኝ ሰሚ ችሎት በእነአንዷለም አራጌ ፍርድ ላይ የሰጠው ውሳኔ ፍ/ቤቶች የገዥው ፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚዎች እንጅ ገለልተኛ ተቋማት አለመሆናቸውን ያሳየ ነው ብሎአል።

ፓርቲው  “ሽብርተኝነት በናይጀሪያ፣ በአፍጋኒስታን እና በፓኪስታን በእየለቱ የምንሰማው እንጅ የኢትዮጵያ ችግር አይደለም በማለት ገልጾ የከፍተኛው ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ወጣቱን ፖለቲከኛና ከፍተኛ አመራር አንዱአለም አራጌንና ናትናኤል መኮንን ን ሽብርተኞች እንደሆኑና በሰላማዊ ትግል ሽፋን ሽብርተኝነትን እንሚያራምዱ አድርጎ ያቀረበው ሀተታ የፓርቲውን  ጠንካራ መዋቅር ያላገናዘበ፣ የፓርቲውን መልካም ስም የሚያጎድፍ ነው ብሎአል።  እነ አንዷለምም ሰላማዊ ታጋዮች እንጅ ሽብርተኞች አለመሆናቸውንም ጠቅሷል።

የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የኢህአዴግ የዕድሜ ማራዘሚያና መጠቀሚያ ከመሆን በዘለለ ፋይዳ የሌለው መሆኑን የገለጸው አንድነት፣ በሽብርተኝነት ስም ዜጎችን ማሰር እንዲቆም  እና የፖለቲካና የህሊና እስረኞ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ጠይቋል።

በሌላ ዜና ደግሞ የግንቦት 7 አባል በመሆን የፈንጂ ስልጠና ሰጥተዋል በተባሉት ሻለቃ ማሞ ለማና አቶ አበበ ወንድማገኝ ላይ የቀረበው ክስ ከትላንት በስቲያ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መሰማቱን አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዘግቧል። በእለቱ በተነበበው የክስ መዝገብ ላይ አቶ አበበ ወንድማገኝ፤ በእንግሊዝ ሃገር ከሚገኙት ሻለቃ ማሞ ለማ ጋር በተደጋጋሚ በዱባይና ለንደን በመገኘት የፈንጂ ጥቃት ለማድረስ የሚያስችል ስልጠና በኤርትራ መውሰዳቸውን ያትታል።

አቶ አበበ ግለሰቦችን በመመልመል የትጥቅ ትግል ለማድረግ በማሰልጠን ለሽብር ተግባር ማነሳሳታቸውን የአቃቢ ህግ ክስ አመልክቶ፣  ጥር 15 ቀን 2005 ዓ.ም ቦሌ ሰሚት አካባቢ መኪና ውስጥ 10 “ C4” የተሰኙ ፈንጂዎችንና ማቀጣጠያ ገመዶችን ይዘው ተገኝተዋል ብሏል፡፡ የተከሳሽ ጠበቃ ባቀረቡት መቃወሚያ፤ የአቃቤ ህግ ክስ በየትኛው አዋጅ እንደቀረበ ክሱ እንደማያመለክት ጠቁመው፤ ደንበኛቸው የፈንጂ ስልጠና መስጠቱን እንዳልካደ በመግለፅ፤ አቃቤ ህግ ያቀረበው የክስ አንቀፅ እንዲያሻሽል ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ የተከሳሽ ድርጊት በሰው ህይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል እንደነበር የሚያካትት ክስ እንዳቀረበ ገልጿል፡፡ “ተከሳሹ ስልጠና ብቻ ነው የሰጠው” የሚባለው ጉዳይ በማስረጃ የምናረጋግጠው ነው በማለት አቃቤ ህግ አክሎ ገልፀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ብይን ለመስጠት ለፊታችን ሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ጋዜጣው ዘግቧል።