ጥቅምት ፲፩ (አሥራ አንድ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሶማሊያ በጋልካዩ ከተማ ለተነሳው የእርስበርስ ግጭት የኢትዮጵያ መንግስት አደራዳሪ መፍትሄ ሰጪ አካል ሆኖ ሊቀርብ እንደማይችል አንድ ታዋቂ የአገር ሽማግሌ ተናግረዋል። የሶማልያ የአገር ሽማግሌ የሆኑት መሃመድ ሃሰን እንዳሉት ኢትዮጵያ በጋልሙዱ እና ፑትላንድ ክልል ለተነሳው ግጭት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የማደራደር ፍላጎት እንደሌላት ተናግረዋል።
የአገር ሽማግሌው ከሸበሌ ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ በሁለቱ አጎራባች የፑትላንድ እና ጋልማዱክ ክልሎች በአፋጣኝ ችግሮቻቸውን በግልጽ ውይይትና ድርድር በማድረግ ለመፍታት ያደረጉትን ጥረት አድንቀዋል።
የሸበሌ ራዲዮ ቀድሞ የነበረው የአካባቢው ግጭት ወደ ጋልካዩ ከተማ መሸጋገሩን እና የከተማ ነዋሪዎች በስጋት ውስጥ እንዳሉ ዘግቧል። ጋልካዩ ከተማ በሁለት ዞኖች የተከፈለች እና ግማሹ ሰሜናዊ ግዛት በፑትላንድ የሚተዳደር ሲሆን ደቡባዊው ደግሞ በጋልሙድ አስተዳደር የሚተዳደር ነው። አንዳንድ የሶማሊ ፖለቲከኞች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በድፍረት የኢትዮጵያ ጦር አገሪቱን ለቆ እንዲወጣ እየጠየቁ ነው።