የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለኮማንድ ፖስት ሳያሳውቁ ከሃገር እንዳይወጡ ዕገዳ ተጣለ

ኢሳት (ጥቅምት 10 ፥ 2008)

በቅርቡ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለኮማንድ ፖስት ሳያሳውቁ ከሃገር እንዳይወጡ ዕገዳ መጣሉን የኢሳት ምንጮች ገለጹ። ለህዝብ ይፋ በሆነው የአፈጻጸም መመሪያ ላይ በግልፅ ባይጠቀስም ኮማንድ ፖስቱ ሳያሳውቅ ከሃገር መውጣት አይችሉም።

ዕሁድ መስከረም 29, 2009 ይፋ የሆነውና ከመስከረም 28 ጀምሮ ተግባራዊ መሆኑ የተገለፀው፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በመላዋ ኢትዮጵያ ስራ ላይ መዋሉ ይታወቃል። ይህንን የሚያስጽም መመሪያ ቅዳሜ ጥቅምት 5 ፥ 2009 ይፋ ቢደረግም፣ የመንግስት ባለስልጣናትን የተመለከተው የማስፈጸሚያ ክፍል ተቆርጦ በውስጣዊ መመሪያነት ተገድቧል።

ኢትዮጵያውያን በምልክት ቋንቋ መነጋገርን ወይንም ምልክት ማሳየትን ጨምሮ በሚናገሩት ብቻ ሳይሆን በሚያዩትና በሚሰሙት ነገር ላይ ጭምር ገደብ የጣለው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአዲስ አበባ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ከአዲስ አበባ ከ40 ኪ/ሜትር የበለጠ መንገድ ለመጓዝ ከፈለጉ ለኮማንድ ፖስቱ ማሳወቅ ግዴታቸው መሆኑንም አስቀምጧል። በትምህርት ተቋማት ሌላው ቀርቶ በመንፈሳዊ ስፍራዎች ጭምር በሚደረጉ ሃይማኖታዊ ስብከቶች ላይ ጭምር ገደብ የሚጥለው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአፈጻጸም መመሪያ ከህዝቡ ግልጽ ተቃውሞ እንደገጠመው በኦሮሚያ ክልል በሜታ ሮቢ በአንድ አጋዚ ወታደር በተገደለ የ9 አመት ተማሪ ስነስርዓት እንዲሁም በጎንደር ከተማ ቢያንስ ለሁለት ቀናት በቀጠለው አድማ ታውቋል።