(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 5/2010) የስዊዲን መንግስት የኢትዮጵያን አምባሳደር ጠርቶ ማነጋገሩ ተገለጸ።
የስዊዲን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አምባሳደሩን የጠራው በቂሊንጦ እስር ቤት በሚገኙት በዶክተር ፍቅሩ ማሩ ጉዳይ ላይ ለማነጋገር መሆኑን የስዊዲን ጋዜጦች ዘግበዋል።
በስዊዲን የኢትዮጵያ አምባሳደር ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ስለተጓተተው የዶክተር ፍቅሩ ማሩ የፍርድ ቤት ጉዳይ ቀርበው እንዲያብራሩ ተጠይቀዋል።
ስዊዲን በዶክተሩ የፍርድ ቤት መራዘም ምክንያት በግልጽ ቅሬታ እንዳደረባት ለአምባሳደሩ ማሳወቋን ጋዜጦቹ ጠቅሰዋል።
የልብ ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ ላለፉት አምስት ዓመታት በእስር ላይ ናቸው።
ቀረጥ ያልተከፈለበት ዕቃ ወደ ሀገር ቤት አስገብተዋል ከሚለው የመጀመሪያው ክስ ነጻ ቢሆኑም ከእስር ሊለቀቁ አልቻሉም።
እዚያው እስር ቤት እያሉ የእሳት ቃጠሎ ይነሳና በርካታ ሰዎች ይሞታሉ።
በአገዛዙ ደህንነቶች በተቀናበረና የተወሰኑ ፖለቲከኞችን ለመግደል ታቅዶ ለተፈጸመው የእሳት ቃጠሎ ተጠያቂ ተብለው ሌላ ፋይል ተከፈተባቸው።
በህይወት የተረፉና በወቅቱ ሁኔታውን በአንደኛ ደረጃ ምስክርነት የገለጹ እማኞች የቂሊንጦ ቃጠሎ በደህንነት መስሪያ ቤቱ የተቀነባበረ ነበር።
ነፍሳቸውን ለማትረፍ ከቃጠሎ የሚያመልጡትን በጥይት የገደሏቸው መሆኑን ከሆስፒታል የቀረበው ማስረጃ አረጋግጧል።
አገዛዙ ሰለባዎችን ተከሳሽ አድርጎ በእስር ቤት ማቆየቱ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በእጅጉ ያወገዙት መሆኑ የሚታወስ ነው።
ዶክተር ፍቅሩ ማሩ በቂሊንጦው የእሳት ቃጠሎ እጃችሁ አለበት ተብለው በፍርድ ቤት ሲመላለሱ አመታት ተቆጥሯል።
እስከአሁን የቀረበ ምስክር ግን አልተገኘም።
በቅርቡ በነበረ ችሎት ላይ ስልኩን አውጥቶ የቪዲዮ ጌም ለሚጫወተው አቃቤ ህግ ‘’አንተ ጌም ተጫወት። እኔ ወደ እስር ቤት ተመልሼ ከአይጥና ከትኋን ጋር እጫወታለሁ’’ በማለት ዶክተር ፍቅሩ ማሩ የተናገሩት የብዙዎችን ስሜት ነክቷል።
እዚህ እስር ቤት ከምቀመጥ በፖሊስ አጀብ ወጥቼ ህሙማንን ለማከም ይፈቀድልኝ በማለትም መጠየቃቸው የሚታወስ ነው።
በዜግነት ስውዲናዊ የሆኑት ዶክተር ፍቅሩ ፍትህ እንዲያገኙ ከየአቅጣጫው ግፊት ቢደረግም አገዛዙ ምላሽ ሊሰጥ አልቻለም።
በተለይም ዜጋዋ አስቸኳይ ፍትህ እንዲያገኙ ስትጠይቅ የቆየችው ስዊዲን ባለፈው ሰኞ የነበረው ችሎት በቀጠሮ ለሚያዚያ 24 መተላለፉ ሲታወቅ በሀገሯ ያሉትን የህወሀት መንግስት አምባሳደርን መጥራቷ ነው የተገለጸው።
ትላንት በስዊዲን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የተጠሩት የህወሀት መንግስት አምባሳደር ፕሮፌሰር መርጋ በቃና መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የስዊዲን ጋዜጦች እንደዘገቡት አምባሳደር መርጋ በቃና ተጠርተው ስለ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ የፍርድ ሂደት መጓተት ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል።
ስዊዲን ጉዳዩ በብርቱ እንዳሳሰባት፣ በሰኞው ችሎት የፍርድ ሂደቱ አንድ ርምጃ ወደፊት ይሄዳል ብላ ተስፋ አድርጋ እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች ለተጨማሪ ቀን መራዘሙ እንዳስቆጣት ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ተጠርተው ስለሰጡት ማብራሪያ ዝርዝር መረጃ አልወጣም።
ሆኖም ስዊዲን የፍርድ ሂደቱ በአስቸኳይ እንዲጠናቀቅ ፍላጎቷ መሆኑን ለህወሀት መንግስት አምባሳደር ማሳወቋ ተገልጿል።
አምባሳደሩ የተጠሩበት የህወሀት አገዛዝ በጉዳዩ ላይ የሰጠው ማብራሪያ የለም።