ለዋልድቦ መነኮሳት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 5/2010) በእስር ላይ የሚገኙት የዋልድቦ መነኮሳት የክህነት ልብሳቸውን እንዲያወልቁ መገደዳቸውን ተከትሎ አቤት በማለታቸው ለውሳኔ ዛሬ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቢደረግም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን አላየነውም በሚል ለመጋቢት 10 /2010 ተለዋጭ ቀጥሮ መስጠቱ ታወቀ።

አባ ገብረኢየሱስ ያሉበት ሁኔታም አሳሳቢ መሆኑ ተገልጿል።

በመነኮሳቱ ጉዳይ ላይ ቤተክርስቲያኒቱም ሆነች ምእመናኑ ዝም ማለታቸው አነጋጋሪ ጉዳይ መሆኑ ታውቋል።

ሁለት ግዜ በምህረት ይለቀቃሉ ተብሎ ነገር ግን የፍርድ ሂደታቸው የቀጠለው የዋልድባ መነኮሳት ጉዳይ ዛሬም ፍርድ ቤቱ ለሌላ ግዜ ቀጠሮ ሰቷቸው ተመልሰዋል።

የእምነት ለብሳችንን አናወልቅም በማለታቸው ከፍተኛ ግፍና የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚደርስባቸው መነኮሳቱ በአንድ ለብስ ከአንድ ዓመት በላይ መቆየታቸውን አመልክተው እንደነበርም የሚታወስ ነው።

ህወሃት መራሹ መንግስት በልማት ሰበብ በዋልድባ ገዳም ላይ የሚያደርሰውን  ጥፋት በመቃወማቸው ለእስር የተዳረጉት መነኮሳቱ በሽብርተኝነት ተከሰው ፍርድ ቤት እየተመላለሱ ይገኛሉ።

መነኮሳቱ ለእምነታቸው ክብር ሲሉ ስቃይና መከራው እየተፈራረቀባቸው እንደሆነ ጉዳያቸውን በቅርበት የሚከታተሉ አካላት ለኢሳት ተናግረዋል።

በማዕከላዊና በቂሊንጦ እስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ እና ሰቆቃ እንደደረሰባቸው ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውንም አስታውሰዋል።

ግፍና መከራው አሁንም ቀጥሏል የሚሉት ምንጮች በተለይ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና የሚመለከታቸው አካላት ብሎም ምእመናኑ ዝም ማለታቸው አስገራሚ ሆኗል ሲሉ ያክላሉ

ሁለቱ አባቶች የእምነት ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ሲገዳዱ አሻፈረኝ በማለታቸው መሬት ለመሬት ሲጎተቱ የቤተክርስቲያኒቱ የበላይ የሚባለው አካል አያገባኝም በሚል ስሜት ዝምታን መምረጡ ተገቢ አይደለም የሚሉ ወግኖች ወቀሳቸውን አድርሰዋል።

እነዚህ አባቶች ጥፋት እንኳን አለባቸው ቢባል የእምነት መገለጫቸው የሆነውን ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ሲገደዱ ቢያንስ ቤተክርስቲያኒቱ ልትቃወም ይገባ ነበር የሚሉት ወገኖች አሁን ለእምነቱ ከብር የሚጨነቅ ማንኛውም አካል ከጎናቸው ሊቆም ይገባል በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል ።