የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል ዘመቻ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉ ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 5/2010) በመላ ኢትዮጵያ የተጠራው የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል ዘመቻ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉ ታወቀ።

ዛሬም ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎችና ሊጭኑ በጉዞ ላይ የነበሩ ከባድ ተሽከርካሪዎች በየመንገድ ዳሩ ቆመው እንደሚታዩም ተገልጿል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በሱዳን በኩል የሚገባው የነዳጅ ስርጭትም ከፍተኛ መስተጓጎል እንደተፈጠረበት የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የተጠራውን ዘመቻ በመጣስ ሲንቀሳቀስ የነበረ ተሽከርካሪ በጎጃም አማኑዔል በተባለ አካባቢ ከጫነው ነዳጅ ጋር መቃጠሉ ታውቋል።

አገዛዙ ግን ምንም የተፈጠረ ችግር የለም፣ በቂ ነዳጅ ስላለ ህብረተሰቡ ያለስጋት እንዲጠቀም ጥሪ አድርጓል።

እስከመጋቢት 10 የተጠራው የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል ዘመቻ በሁለተኛ ቀኑ ማደያዎችን ጾም እንዲውሉ ማድረጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የዘመቻው ተጽዕኖ ጎልቶ በሚታይባት አዲስ አበባ ዛሬም የነዳጅ ማደያ ስፍራዎች በአብዛኛው ጭር ብለው መዋላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ከጎተራ ሳሪስ ድረስ ባለው መንገድ ላይ በርካታ የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆነው ይታያሉ።

ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ በሚወስደው መንገድ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች የቆሙ የነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪዎች እንደሚታዩም በፎቶግራፍና በቪዲዮ የተደገፉ መረጃዎች አመልክተዋል።

የአንድ ሳምንቱ ዘመቻ በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ተጽዕኖው ጎልቶ እንደሚታይ ተገልጿል።

ከሱዳን በመተማ ነጋዴ ባህር ሸዲ ጭልጋ አዘዞ አድርጎ የሚገባው የነዳጅ ቦቴ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መቆሙ ታውቋል።

በባህርዳር ድባንቄ መድሃኒዓለም ፊት ለፊት የሚገኘው የመጠባበቂያና ማጠራቀሚያ የነዳጅ ዲፖ የሚወጣም ሆነ የሚገባ ነዳጅ ጫኝ (ቦቴ) ተሽከርካሪ አይታይም።

ለምዕራብ ዕዝ ዋና የነዳጅ አቅርቦት የሚውለው በሽምብጥ አካባቢ ከሚገኘው የነዳጅ ዲፖ በተጨማሪ የወታደር ሃይል እየተጠበቀ ነው።

ነዳጅ ይዘው ወደ መከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት መኮድ የሚሄዱም  ሆነ ከሱዳን ጭነው የመጡ የነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪዎች ከትላንት ጀምሮ አይታዩም።

ዛሬ ጠዋት ለወታደራዊ ተሽከርካሪዎች የሚውል ነዳጅ ከዲፖው በበርሜል እየተቀዳ በፒካፕ መኪና ተጭኖ ወደ መኮድ መሄዱ ታውቋል።

ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ነዳጅ የጫኑ ቦቴ ተሽከርካሪዎች መተማ ዩሃንስ ከተማ ላይ በብዛት ቆመዋል።

ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎችን በወታደራዊ ጥበቃ ለማጓጓዝ ሙከራ እየተደረገ ቢሆንም ሊሳካ እንዳልቻለ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በሌላ በኩል ለአባይ ግድብ በሳምንት 3 ተሳቢ ነዳጅ ይላክ የነበረ ሲሆን የተአቅቦ አድማው ከተጠራ ወዲህ ግን ትላንትናና ዛሬ ወደ ግድቡ የተጓዘ የነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪ እንደሌለ ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም ትላንት የተጠራውን ዘመቻ ባለመቀበል ሲንቀሳቀስ የነበረ አንድ የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪ መቃጠሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በምስራቅ ጎጃም አማኑዔል በተባለ አካባቢ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ከጫነው ነዳጅ ጋር የጋየው የነዳጅ ቦቴ መኪና ከህዝብ የተላለፈን ጥሪ ወደ ጎን በማድረጉ ርምጃው እንደተወሰደበት ተገልጿል።

ለአንድ ሳምንት የተጠራው የነዳጅ አቅርቦትን የማስተጓጎል ዘመቻ በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩ እየተገለጸ ባለበት በዚህን ወቅት ባለስልጣናቱ  ዘመቻው የፈጠረው ችግር የለም እያሉ ነው።

አሽከርካሪዎች ጥቃት ይደርስብናል በሚል ስጋት ውስጥ በመሆናቸው ወደ አዲስ አበባ የገቡት በኮማንድ ፖስቱ ታጅበው መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።