ሚያዚያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሳውና ለሦስት ቀናት የዘለቀው የሰደድ እሳት ባካባቢው ሕዝብ ርብርብ መቆሙተገለጠ።
ሰደድ እሳቱ ከፓርኩ ይዞታ 15 ኪ.ሜ. ያህል ዘልቆ ጥፋት አድርሷል።ኢሳት ዛሬ ያነጋገራቸው የደባርቅ ከተማ ነዋሪ መንግሥት በወቅቱ የወሰደው የማጥፋት ሙከራ ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ እሳቱን ለመቆጣጠር ሦስት ቀን ሊወስድበት ችሏል ብለዋል።
በሌላ በኩል ግን ዛሬ በተለይ ከኢሳት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የደባርቅ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በለጠ፤ እሳቱን ለማጥፋት የተረባረበው ሕዝቡ ብቻውን አይደለም፤ መንግሥት ጭምር ነው ብለዋል።
የወረዳው አስተዳዳሪ የእሳቱን መንስዔ አላወቅንም ያሉ ሲሆን የጠፋውን ጥፋት በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄ ግምገማ እየተደረገ በመሆኑ ይህን ያህል ጥፋት ደርሷል ለማለት አልችልም ብለዋል።
የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ብቻ የሚኖሩና በሌላው ዓለም የማይገኙ እንደ ቀይ ቀበሮ፣ ዋልያ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ የመሳሰሉ እንስሳት እንዲሁም አዕዋፍና እፅዋት የሚገኙበት ፓርክ መሆኑ ይታወቃል።