(ኢሳት ዜና–ሕዳር 25/2010)
የሱዳን ወታደሮች 40 ኪሎ ሜትር ያህል ድንበር ጥሰው ወደ ኢትዮጵያ ክልል በመግባት ሰብል ማቃጠላቸውን የኢሳት ምንጮች አጋለጡ።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ወታደሮቹ በምዕራብ አርማጭሆ አብርሃ ጅራ ኮርመር እስከሚባል አካባቢ ዘልቀው መግባታቸው ታውቋል።
አሰሪ የተባለውን የኢትዮጵያ መሬት መቆጣጠራቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
የህወሃት መከላከያ ሰራዊት ከባህርዳርና መተማ ተነስቶ ወደ ስፍራው እየተጓዘ መሆኑ ቢታወቅም የመከላከያ ሰራዊቱ አካሄድ ግን ወታደሮቹን ለማስወጣት ይሁን የአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ለማጥቃት የታወቀ ነገር የለም ተብሏል።
የአካባቢው አርሶአደሮች ግን ትጥቃቸውን ይዘው ድንበራቸውን መመከት መጀመራቸው ታውቋል።
ሰፋፊ መሬቶች ከጎንደር አርሶ አደር ተነጥቀው ለሱዳን ተሰጡ የሚለው ወሬ የሚያጠራጥር ነው ይላሉ የአካባቢው ነዋሪዎች።
ምክንያታቸው ደግሞ በየጊዜው ልክ እንደራሳቸው ቤት ገባ ወጣ የሚሉትና ያሻቸውን የሚያደርጉት የሱዳን ወታደሮች ጉዳይ ግራ ቢያጋባቸው ነው።
ዛሬ ላይ ከአካባቢው የተሰማው ዜናም ይህንን ያረጋገጠ ሆኗል።
ኢሳት ከስፍራው እንዳገኘው መረጃ ከሆነ የሱዳን ወታደሮች 40 ኪሎ ሜትር ያህል የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው መግባታቸው ታውቋል።
የሱዳን ወታደሮች በምዕራብ አርማጭሆ አብርሃ ጅራ ኮርመር እስከሚባለው አካባቢ ዘልቀው መግባታቸውንና አሰሪ የተባለውን የኢትዮጵያ መሬት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን ነው አንድ ሁኔታውን ያዩ የአካባቢው ነዋሪ የገለጹልን።
ነዋሪው እንደሚሉት ወታደሮቹ የገቡበት መሬት ቀድሞውኑ የኢትዮጵያ መሬት እንደሆነ ነው የሚታወቀው።
ነገር ግን ወታደሮቹ በራሳችን መሬት ላይ እንዲህ አይነቱን ድርጊት ሲፈጽሙ የመጀመሪያቸው አይደለም ይላሉ።ወቅትን እየጠበቁ የሚያደርጉት ነው ሲሉም ያክላሉ።
ወታደሮቹ የህወሃትን አገዛዝ የተማመኑና ምንም አታመጡም ያሉ ይመስላል ወደ ሀገራችን ድንበር 40 ኪሎ ሜትር ያህል በመግባት እስከ ምዕራብ አርማጭሆ ድረስ ዘልቀዋል።
ጉዳዩን የሰማው የህወሃት መንግስትም በባህርዳርና መተማ ያለውን የመከላከያ ሰራዊት ወደ ስፍራው ማንቀሳቀሱን ነዋሪው ገልጸዋል።
የህወሃት አገዛዝ ወታደሮቹን ውጡ ይበላቸው አይበላቸው ባናውቅም አሁን ላይ ግን ሰብልን ከማቃጠል አልፈው ሰው ላይ እስከመተኮስ ደርሰዋል ሲሉ ይናገራሉ።
የህወሃት መከላከያ ሰራዊት ከባህርዳርና መተማ ተነስቶ ወደ ስፍራው እየተጓዘ መሆኑ ቢታወቅም የመከላከያ ሰራዊቱ አካሄድ ግን ወታደሮቹን ለማስወጣት ይሁን የአካባቢውን ነዋሪዎች ለማጥቃት የታወቀ ነገር የለም ተብሏል።
እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ የመከላከያ ሰራዊቱ ወደ ስፍራው የሚሄደው ድንበር ለማስጠበቅ ነው የሚል እምነት የለንም ።
የመከላከያ ሰራዊቱ በሱዳን ወታደሮች ድንበር ጥሶ ገብቶ ሰብል ማቃጠልና አርሶ አደሩ ላይ ላይ ጉዳት የማድረሱ ጉዳይ ላይ ደስተኛ አለመሆኑን ማወቅ ችለናል ብለዋል።