የሰሜንና የደቡብ ሱዳን ውዝግብ

የካቲት 27 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሰሜንና ደቡብ ሱዳን፤ በነዳጅ ሀብቷ በበለፀገችው በኮርዶፋን ግዛት ዙሪያ የፈጠሩትን  የይገባኛል ውዝግብ ለመፍታት፤ በኢትዮጵያ ሸምጋይነት አዲስ አበባ ውስጥ ድርድራቸውን ለመጀመር በተዘጋጁበት ጊዜ የአልበሽር መንግስት- ደቡብ ሱዳንን ለመውጋት መዘጋጀቱ ተዘገበ።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ልዑክ የሚዲያ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤ የሱዳን መንግስት ከደቡብ ሱዳን ጋር የፈጠረውን ውዝግብ በድርድር ለመፍታት በገለፀበት ማግስት ኬንያ፤ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ሰሞኑን በጋራ ተስማምተው ይፋ ያደረጉት የላሙ ፕሮጀክት ሳያስቆጣው አልቀረም።

የደቡብ ሱዳን የቀድሞ ዕቅድ፤ ከላሙ ወደ ጂቢቲ የሚዘረጋው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ በሰሜን ሱዳን በኩል አድርጎ ወደ ጅቡቲ እንደሚደርስ የሚያመለክት የነበረ ሲሆን፤ ኬንያ፣ኢትዮጵያና ሱዳን ሰሞኑን ይፋ ባደረጉት ፕሮጀክት ግን፤ ከላሙ ወደ ጅቡቲ ሚዘረጋው የነዳጅ ማስላለፊያ ቧንቧ- በኢትዮጵያ በኩል እንደሚያልፍ የሚያመለክት ነው።

ሰሜን ሱዳንን ያገለለው የሦስቱ አገሮች ስምምነት የአልበሽርን አስተዳደር ክፉኛ ማስቆጣቱ እየተነገረ ከመሆኑም በላይ፤  ሰሜን ሱዳን- ከቀድሞ ግዛቷና ከአዲሷ ነፃ አገር ከደቡብ ሱዳን ጋር ጦርነት ለመጀመር መዘጋጀቷ  እየተሰማ ነው።

በመሆኑም በአዲስ አበባ ይጀመራል የተባለው የሁለቱ ሱዳኖች ድርድር፤ ለመርሀ-ግብር ማሟያ ብቻ የሚደረግ እንጂ ምንም ውጤት ሊኖረው እንደማይችል የሱዳን ጋዜጦች ከወዲሁ ጽፈዋል።

የላሙ ፕሮጀክት ከዚህም ባሻገር ፤ በጥርጣሬ የተሞላውንና በቋፍ ላይ የሚገኘውን  የኢትዮጵያንና የሱዳንን ግንኙነት ጨርሶ በማበላሸት- ኢትዮጵያ  በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ያላትን ቦታ  ያሳጣታል የሚሉ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።

በቅርቡ ዊክ ሊክስ ይፋ ባደረገው መረጃ፤  የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በዓለማቀፉ ፍርድ ቤት እንዲከሰሱ ፤የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ  ለአሜሪካ ባለስልጣናት ነገር ሲያሳልጡ እንደነበር ማጋለጡ አይዘነጋም።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide