(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 9/2009) በባህር ዳር ከተማ ነሃሴ አንድ ቀን የዋለውን የሰማዕታት ቀን አክብራችኋል በሚል በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ ታዋቂ ነጋዴዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች ፍርድ ቤት እየቀረቡ ናቸው፡፡
በከተማዋ በሚገኙ የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙት ነጋዴዎች በባህር ዳር ከተማ ፍርድ ቤቶች ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ቀርቦባቸዋል ፡፡
ክሱ የቀረበላቸው አንዲት ሴት ዳኛ የንግድ መደብርን መዝጋት መብት ነው በማለታቸው በችሎቱ የተገኙት ፖሊሶች ወንጀሉን ከአድማ ሕገመንግስትን በሀይል ለመቀየር ወደ መሞከር በሚል መቀየራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ፖሊስ ባቀረበው የምርመራ መዝገብ መሰረት “ ነሃሴ 1 ቀን 2009 ዓ ም. የንግድ ቤታቸውን ዘግተዋል” የሚለው ውንጀላ በእስረኞቹ ጠበቆች ተቃውሞ ቀርቦበታል። የንግድ ቤትን መዝጋት ህገመንግስታዊ መብት በመሆኑ ሊያስከስስም ሆነ ሊያስቀጣ ስለማይገባ ደንበኞቻችን በየዋስትና መብታቸው ተጠብቆ በውጭ ይከራከሩ በሚል የተከሳሽ ጠበቆች ተከራክረዋል፡፡
በችሎቱ የተሰየሙት የሴት ዳኛም ፖሊስ ያቀረበው የምርመራ መዝገብ ምንም ዓይነት ወንጀል ባለመሆኑ ተከሳሾች ሌላ ወንጀል ካልሰሩ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ በውጭ መከታተል ይችላሉ በማለት የፖሊስን የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ እንደማይቀበሉት ተናግረዋል፡፡
በሁኔታው ግራ የተጋባው የፖሊስ መርማሪ በርቀት የተሰጠውን የአለቆቹን ትዕዛዝ ለማስፈጸም ፍርድ ቤቱን በጽሁፍ ባልቀረበ ተጨማሪ ክስ “ህገ መንግስቱን ለመናድ በመሞከር” የሚል ተጨማሪ ጉዳይ አለኝ በማለት አስመዝግቦ በማቅረብ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡
በችሎቱ የተሰየሙት ዳኛም ምንም እንኳን ሂደቱ ከህጉ ውጭ ቢሆንም ፖሊስ ምርመራየን እስካጣራ መረጃ እንዳያጠፉብኝ ብሎ በመጠየቁ የአስራ አራት ቀን ሳይሆን የአምስት ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቻለሁ በማለት የእለቱን ችሎት ዘግተዋል፡፡ጉዳዩን ለመከታተል በፍርድ ቤቱ በመቶዎች የሚቆጠር ህዝብ ተገኝቷል።
የዕለቱ ዳኛ ወደ ችሎት የገቡትን የታሳሪ ቤተሰቦች ሳይከለክሉ የፍርዱን ሂደት እንደዲከታተሉ ማድረጋቸውም በቦታው በተገኙ ቤተሰቦችና ታዛቢዎች አድናቆትን አግኝተዋል፡፡
በተለያዩ እስር ቤቶች የታሰሩት ከ200 በላይ የሚሆኑ ከፍተኛ ባለሃብቶች፣መለስተኛ የችርቻሮ ሱቅ ባለቤቶች ይገኙበታል።
በባለሃብቶች ድርጊት የተበሳጩት የብአዴን/ህወሃት አመራሮች፣ በነጋዴዎች ላይ የማያዳግም ያሉት እርምጃ እንዲወሰድባቸው እየወተወቱ ነው። ከግብር ጋር በተያያዘ ከተደረጉት የስራ ማቆም አድማዎች ሁሉ በላይ ያበሳጫቸው ለነጻነት ሰማዓታቱ የተደረገው የስራ ማቆም አድማ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል።
ይሕ በእንዲህ እንዳለም የቦምብ ጥቃት ተፈጽሞበታል በተባለው ካሪቡ ካፌና አካባቢው ፖሊስ ድርጊቱ እንዴት እንደተፈጸመ የሚተርክ የቪዲዮ ቀረጻ ሲያደርግ ውሏል።ይሕንኑ ኦፕሬሽን የሚመሩትም ግርማ ፈንታሁን የሚባል የመረጃና ደህንነት ሰራተኛና የማነ ግርማይ የተባለ የሕወህት ወኪል መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።ለቀረጻው ሲባል ካሪቡ ካፌ ዝግ ሆኖ መዋሉ ነው የተነገረው።የአገዛዙ ፖሊሶች ጥቃቱን ያደረሱትን ተጠርጣሪዎች ይዘናል ቢሉም አሁንም ድርጊቱን ማን ፈጸመው በሚሉ ጉዳዮች ተጥምደው የቆሰሉትን ግልሰቦችና የአካባቢው ነዋሪዎቹን እያንገላቱ መሆናቸው ተነግሯል።የቦምብ ጥቃቱን ፈጽመናል ብለው ቀረጻ እንዲደረግባቸው የተመረጡ ወጣቶች ወደ ስፍራው ከተወሰዱ በኋላ አንደኛው እምቢ በማለቱ ቀረጻው መቋረጡን ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያመልክታል።