ህዳር ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-መንግስት በበኩሉ ሐውልቱ ለደህንነቱ ሲል ከተነሳ በሁዋላ ወደነበረበት ስፍራ ይመለሳል እያለ ነው።
በአዲስ አበባ ውስጥ ሊሠራ በታቀደ የ ከተማ ውስጥ የባቡር ሀዲድ ሥራ ምክንያት የዓፄ ምኒልክና የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሊፈርሱ የመቻላቸው ወሬ አስቀድሞ የሾለከው ፤ለምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ቅርበት ካላቸው ምንጮች ነው።
እነዚህ የዘርፉ ሙያተኞች በ አምስት ዓመቱ የልማትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት በ አዲስ አበባ ውስጥ ሊዘረጋ የታሰበው የባቡር ሀዲድ ፕላን የዳጋማዊ አፄ ምኒልክንና የ አቡነ ጴጥሮስን ሐውልት እንደሚነካ በመጥቀስ፤ በተለይ የጣሊያንን ወረራ አልባርክም በማለታቸው ሳቢያ በመትረየስ ተደብድበው የተገደሉት የ አቡነ-ጴጥሮስ ሐውልት ሙሉ በሙሉ እንደሚፈርስ ተናግረዋል። ዜናውን የሰሙ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ ማህበራዊ ገፆች ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀምረዋል።
በጽሁፍ የተቃውሞ ሀሳባቸውን ከገለጹት መካከል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አንዱ ነው።
“ስለ ባቡር በመዝፈን ከመቶ ዓመት በላይ ያሳለፍን ሕዝቦች የከተማ ባቡር ማግኘታችንን በዕልልታ የምንቀበለው ነገር ነው”ያለው ዳንኤል፤” ዘግይተን ይሆናል እንጂ አልቸኮልንም፡፡ ሥራው በቁርጠኝነት መጀመሩና ከወሬ አልፎ ሲተገበር ማየታችንም እሰዬው የሚያሰኝ ሆኗል”ብሏል።
“ግን ደግሞ ጥያቄ አለን..”በማለት ጽሁፉን የቀጠለው ዳንኤል፦ “ይህ የባቡር መሥመር የአቡነ ጴጥሮስንና የዐፄ ምኒሊክን ሐውልት እንዲነሡ ያደርጋል?
ለዚህ ጥያቄ ምላሹ ‹አዎን› ከሆነ ስለ ባቡሩ የሚኖረን ግምት ይለያል፡፡ ኢትዮጵያን እናሳድጋለን ስንል ያሳደጓትን እየዘነጋንና መታሰቢያቸውን እያፈረስን መሆን የለበትም”ብሏል።
‹በማን ላይ ቆመሽ እግዜርን ታሚያለሽ› አለ ያገሬ ሰው ” በማለት የቀጠለው ዳንኤል ፦”የምናመጣው አዲስ ነገር- ባለን ላይ የሚጨመር እንጂ ያለንን የሚያጠፋ መሆን የለበትም፡፡ መኪና ያስፈልገናል፣ ግን እግር የሚቆርጥ መሆን የለበትም፡፡ ወደድንም ጠላንም ይህች ሀገር የታሪክና የቅርስ ሀገር ናት፡፡
ይህ ታሪኳና ቅርሷ ደግሞ የህልውናዋም ምንጭና መሰንበቻም ጭምር ነው፡፡ ይህን ታሪክና ቅርስ እያጠፉና እያበላሹ የሚመጣ ለውጥ አንገት ቆርጦ ፀጉርን እንደማስተካከል ነው የሚቆጠረው፡፡ እናም የሚመለከታቸው ሁሉ ወደ ርምጃ ከመግባታቸው በፊት ሦስት ጊዜ ሊያስቡ ይገባል፡፡” ብሏል።
ሌሎችም በርካታ ኢትዮጵያውያን ጠንካራ ተቃውሞዋቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
መንግስት በበኩሉ በባቡር ሀዲድ ምክንያት የዳግማዊ አጼ ምኒልክና የ አቡነ-ጴጥሮስ ሐውልት ይፈርሳል የሚለው ወሬ ከ እውነት፡የራቀ ነው በማለት መግለጫ አውጥቷል።
የሀዲዱ ግንባታ የምኒልክን ሐውልት ጭራሽ አይነካውም ያለው የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የ አቡነ-ጴጥሮስ ሐውልት ግን ለደህንነቱ ሲል ከተነሳ በሁዋላ እንደገና በነበረበት ስፍራ ይቀመጣል ብሏል።
የኮፖሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ አበበ ፤የባቡር መተላለፊያ ዋሻ ከሃውልቱ ስር ስለሚገነባ ፤ ግንባታው እስኪያልቅ ድረስ ሃውልቱ ለጥቂት ጊዜ ይነሳና ከዋሻው መጠናቀቅ በኋላ ወደ ቦታው ይመለሳል ብለዋል-ራዲዮ ፋና እንደዘገበው።
“መቼም የመጀመርያውን ባቡር ያስገቡትን የዐፄ ምኒሊክን ሐውልት አፍርሶ ባቡር እናስገባ ማለት የታሪክ ምጸት ነው፡፡ ለነጻነት የተሠውትን የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ነቅሎ በባቡር ላይ በነጻነት ለመሄድ መከጀል ግፍ መሥራት ነው የሚሆነው” ያለው ዳንኤል ክብረት፤ምላሹ ‹አይደለም› ከሆነ ደግሞ እሰዬው፡፡ ግን አሁን በሐውልቶቹ አጠገብ የሚከናወነው ቁፋሮ ወደ መሠረታቸው እየሄደ ነው፡፡ እንደሚሰማውም የባቡሩ መሥመር በሐውልቶቹ ሥር የሚዘረጋ ነው፡፡ ታድያ የሐውልቶቹ ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? ለሕዝቡስ ግልጽ ማብራርያ የማይሰጠው ለምንድን ነው? ‹ለጊዜው ተነሥተው በኋላ ይመለሳሉ› የሚል መረጃም እየተሰማ ነው፡፡ ለጊዜውስ ተነሥተው የት ነው የሚሄዱት? በኋላስ በምን ሁኔታ ነው የሚመለሱት? ታሪካዊ ቦታቸውንስ ይለቃሉ?ግልጽ መልስ ያስፈልጋል፡፡>>በማለት መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ለህዝቡ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል