የሰመጉና የሴቶች የህግ ባለሙያዎች ማህበር ገንዘብ እንዲወረስ የተወሰነው ውሳኔ ጸና

ጥቅምት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት፤ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሴቶች የህግ ባለሙያዎች ማህበር ገንዘብ እንዲታገድና እንዲወረስ በበታች ፍ/ቤቶች የተወሰነውን ውሳኔ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ አጸና።

የአገሪቱ ከፍተኛው የፍትህ አካል የሆነው ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚው ችሎት፤ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ባለስልጣን 20 ሚሊዮን ብር የሚደርሰውን የሁለቱን ድርጅቶች ገንዘብ እንዲታገድና እንዲወረስ የወሰነውና ቦርዱና ከፍተኛው ፍ/ቤት የደገፉትን ውሳኔ፤ መሰረታዊ ሕግ ስህተት የለበትም ሲል ወስኗል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ባለስልጣን፤ ከሁለት አመታት በፊት የሰመጉን 9 ሚሊዮን ብርና የሴቶች የህግ ባለሙያ ድርጅት ለድርጅቱ ጽ/ቤት ግንባታ ያሰባሰበውን 10 ሚሊዮን ብር ከተለያዩ የአገሪቱ ንግድ ባንኮች እንዲታገዱ መወሰኑን ያስታወሱት አቶ እንዳልካቸው ሞላ፤ አብዛኛውን ብር የሰበሰብነው አዋጁ ከመውጣቱ በፊት፤ የተቀረውን ደግሞ አዋጁ በሰጠው የመሰናዶ አንድ አመት ግዜ ውስጥ ቢሆንም፤ አዋጁን በተጻረረ መልኩ ገንዘቡ እንዲወረስብን የተላለፈውን ውሳኔ፤ ሰበር ሰሚ ፍ/ቤቱ አጽድቆታል ብለዋል።

በ2001 ዓ.ም. የወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 621/2001፤ በሰብአዊ መብትና በመልካም አስተዳደር ላይ የሚሰሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት፤ ከገቢያቸው 10 ከመቶውን ብቻ ከውጭ አገር እንዲያገኙ የሚፈቅድ ሲሆን፤ የተቀረውን ግን ከአገር ቤት ምንጮች ብቻ እንዲሰበስቡ ያዛል።

እንደአቶ እንዳልካቸው ገለጻ፤ አዋጁ ተግባር ላይ እስኪውል ለድርጅቶች የአንድ አመት የመሰናዶ ግዜ ቢሰጥም፤  የበጎ አድራጎትና ማህበራት ባለስልጣን፤ ከአዋጁ በፊትና በአንዱ አመት የችሮታ ግዜ የተሰበሰበውን በአቢሲኒያ፤ በንግድ ባንክና ንብ ባንክ የተቀመጠውን የሰመጉን ገንዘብ አዋጁን ጥሶ የተሰበሰበ ነው በሚል ሰበብ እንዲታገድ ቀደም ሲል ወስኖ ነበር።

የሰመጉን ይግባኝ የሰማው የባለስልጣኑ ቦርድና ከፍተኛው ፍ/ቤት የባለስልጣኑን ውሳኔ አጽንተዋል።

ሰመጉና፤ የሴቶች የህግ ባለሙያዎች ማህበር ለጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ቢሉም፤ በመጨረሻ ጉዳዩን የተመለከተው የጠቅላይ ፍ/ቤቱ ሰበር ሰሚ ችሎት፤ የታች ፍ/ቤትና ቦርዱ ውሳኔዎች መሰረታዊ የሕግ ስህተት የለባቸውም በማለት በድምሩ 20 ሚሊዮን የሚደረስ የሁለቱን ማህበራት ገንዘብ እንዲታገድና እንዲወረስ የተወሰነውን ውሳኔ አጽንቷል።

ኢሳት ያነጋገራቸው የሰመጉ ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ሞላ፤ በዚህ ህግና ውሳኔ ምክንያት ባለፉት ሁለት አመታት ብቻ ከ60 ሰራተኞች ወደ ወደ 12 ሰራተኞች፤ ከ12 ቢሮዎቸም ወደ ሶስት ቢሮዎች እነደቀነሱ ተናግረው፤ ውሳኔው የሰመጉን ስራ እንደሚጎዳው ተናግረዋል።

ሰብአዊ መብቶች አለማቀፋዊ ሆነው ሳለ፤ ከአገር ውጪ ገንዘብ እንዳትቀበሉ ማለት አግባብ አይደለም ሲሉ ተናግረው፤ አቅማቸው በፈቀደ መጠን በአገር ውስጥ ለጋሾች በመረዳት ስራቸውን ለመስራት እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

በአዲሱ የኢትዮጵያ ህግ መሰረት፤ የጠቅላይ ፍርድቤቱ ሰበር ሰሚ ውሳኔዎች የሀገሪቱ የበላይ ህግ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን፤ ወደፊት የሚነሱ ተመሳሳይ ጉዳዮችም በዚህ ውሳኔ መሰረት እንደሚወሰኑ ታውቋል።

ከአቶ እንዳልካቸው ሞላ ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ በዛሬ የኢሳት ሬድዮ ላይ ቀርበዋል።