ወደሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚገቡ ልጃገረዶች መጠን 30 ከመቶ ብቻ ነው

ጥቅምት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በኢትዮጵያ ውስጥ ወደሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚገቡ ሴት ተማሪዎች ቁጥር ከአፍሪካ አማካይ እንኩዋን ያነሰ መሆኑ አሳሳቢ እንደሆነ፤ ፕላን ኢንተርናሽናል የተሰኘው አለማቀፍ ድርጅት ገለጸ።

ድርጅቱ በዚህ ወር ባወጣው የዓለም የልጃገረዶች ሁኔታ የተመለከተ ዘገባ፤ በአንደኛ ደረጃ የተመዘገቡ ሴቶች ቁጥር ከ30 በመቶ ወደ75 በመቶ ቢያድግም፤ ከአንደኛ ደረጃ ወደሁለተኛ ደረጃ የሚሸጋገሩ ልጃገረዶች ቁጥር ግን 20 ከመቶ ብቻ ነው ሲል አትቷል።

ከሰሀራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ወደሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚሸጋገሩ የሴት ተማሪዎች አማካይ መጠን 62 ከመቶ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ግን ከአማካዩ በግማሽ ያነሰ መሆኑ ታውቋል።

እድሜያቸው ከ10-14 አመት ውስጥ ከሚገኘውና ጨርሶ ትምህርት ቤት ገብተው በማያውቁ ልጃገረዶች ቁጥር ኢትዮጵያ ከቢኒ ጊሳዎ ቀጥሎ፤ ከማሊ ጋር በመሆን ከመጨረሻ ሁለተኛ ደረጃ ትገኛለች።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ በ12 አመታቸው ትክክለኛ ወይም ተመጣጣኝ የትምህርት ደረጃ ላይ ያሉ ልጃገረዶች፤ ከመቶ 16 ብቻ እንደሆኑም የፕላን ኢንተርናሽናል ዘገባ ያሳያል። ከ10-14 አመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ፤ 58.5 ከመቶ የሚሆኑት ከ2 እና ከዚያ አመታት በላይ በትምህርት ደረጃቸው እንደዘገዩ ያመለክታል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከቻድና ከቢኒ ጊሳዎ ቀጥላ ከመጨረሻ ሶስተኛ መሆኗ ታውቋል።

በዚህ ሳምንት የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት በኢትዮጵያ ከመሀይምንት የተላቀቁ ሰዎች ቁጥር 28 ከመቶ መድረሱንና ኢትዮጵያ ከ184 አገራት 182ኛ ደረጃ መውጣቷን መናገሩን መዘገባችን ይታወሳል።

ይሁን እንጂ አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መክፈቻ ስብሰባ ላይ የገዢውን ፓርቲ መልእክት ሲያስለላልፉ፤ ባለፉት አመታት የታየው የ11.7 ከመቶ እድገት እንደተደገመና እንደሚደገም፤ እንዲሁም በኢትዮጵያ የጤናና ትምህርት አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋታቸውን መናገራቸው የሚታወስ ሲሆን፤ አቶ ኃ/ማርያምም በፓርላማ ተገንተው ይሄንኑ ማረጋገጣቸውን መዘገባችን ይታወሳል።