ኢሳት ዜና:- አቶ ግርማ ሰይፉ ከአውራምባ ታይምስ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ ሰሞኑን አቶ መለስ በፓርላማ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ከወትሮው በተለየ መልኩ በ አቶ መለስ አስተያዬት ዙሪያ ሀሳባቸውን ለመስጠት እንዳልተፈቀደላቸው ጠቅሰዋል።
“ይህ ነገር መታረም ካልቻለ ምናልባትም ለምክር ቤቱ ጥያቄዎቻችንን አስገብተን እሳቸው መልስ እንዲሰጡና እኛ በቴሌቪዥን ብንከታተል የሚሻል ይመስለኛል”ያሉት አቶ ግርማ፤ “የምክር ቤት አባል መሆኔ ትርጉም የሚኖረው፤በተሰጡት አስተያዬቶች ላይ ሀሳቤን በማንጸባረቅ ስችል ይመስለኛል”ብለዋል።
አቶ ግርማ አክለውም በተደጋጋሚ ጠ/ሚኒስትሩ በተሳሳተ የመነሻ ምክንያት ተንደርድረው ያሻቸውን ዓይነት ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ‘ሃይ!’ ለማለት እንኳን አልተቻለም።‘የለም! እርስዎ ያሉትና እኛ የገባን ይለያያል’ ለማለት እንኳ፤ እድሉን አላገኘንም። ሁኔታው እጅግ አሳፋሪ ነው። የም/ቤት አባልነቴ በቴሌቪዥን ቢሆንልኝ ይሻል ነበር’ ሲሉ ተናግረዋል።
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጋዜጠኞች ላይ የሰነዘሩትን ትችት እንዴት ይመለከቱታል?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ግርማ ከተሳሳተ መነሻ-ምክንያት ተነስተው ወደ አደገኛ ድምዳሜ የሚሄዱበትን አግባብ የሚያሳይ ሌላኛው ጉዳይ ነው”ብለዋል።
“ እርሳቸውን ያበሳጫቸው፤ ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ ብያኔ ከመስጠቱ በፊት ‹የግል ጋዜጠኞች ተከሳሾቹን ነፃ ናቸው ይላሉ› የሚለው ነው” ያሉት ብቸኛው የተቃዋሚ ዕጩ፤ ሰዎች በፍ/ቤት ወንጀለኞች መሆናቸው ተረጋግጦ ወንጀለኛ እስከሚባሉ ጊዜ ድረስ ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠ ከመሆኑ አንፃር፤ ይሄ አባባል በሕግ ፅንሰ-ሃሳብም ሆነ ተግባራዊ አሰራር የሚደገፍ እንጂ የሚያበሳጭ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
አያይዘውም በተቃራኒው ግን የመንግስት ጋዜጠኞች የነዚህ ሰዎች ጉዳይ በፍ/ቤት ሳይረጋገጥ ወንጀለኛ ናቸው ሲሉ ይፈርጇቸዋል። ስለዚህ ‹ጋጠ-ወጥ› መባል ያለባቸው የመንግስት ጋዜጠኞች እያሉ፤ ሰዎችን ነፃ ብለው የሚያስቡትን ‹ጋጠ-ወጥ› ማለት ግን ተገቢ አይመስለኝም”ብለዋል።
አቶ መለስ ፍርድ ቤት ገና ጥፋተኛታቸውን ስላላረጋገጠባቸው ሰዎች “ነፃ ናቸው” ብለው እየፃፉ ነው ያሏቸውን ጋዜጠኞች “ጋጠ-ወጥ” ካሏቸው፤ በዚያው መድረክ ላይ ፦”የታሰሩት ወንጀለኞች ናቸው። አንድም ሰው ያለ ማስረጃ አልታሰረም። ለሁሉም በቂ ማስረጃ አለ” እያሉ ዳኛ ሆነው ፍርድ ሲሰጡና ተፅዕኖ ሲፈጥሩ የነበሩት ራሳቸው መለስ ምን ይሆን የሚባሉት? ሲሉ ታዛቢዎች ጠይቀዋል።