የሜድሮክ ኮንስትራክሽን ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መቱ

ኢሳት ዜና:- ከ 500 በላይ የሚሆኑት የሚድሮክ ጉርድ ሾላ፣ የረር በርና አያት ሳይት መንገድ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ የመቱት፤  ባለፈው ሐሙስ ነው።

ኑሮ ሰማይ በነካበት በአሁኑ ሰዓት የአብዛኞቻችን ደመወዝ ከ 500  ብር ብዙም አይበልጥም የሚሉት እነዚሁ ሠራተኞች፤”‹ከዚህች ኪስ ከማትገባ ደመወዝ ላይ ለታክስና ለዓባይ ግድብ ተቆርጦላት  በእጃችን የምትደርሰን ከቤት ኪራይ እንኳ የማታልፍ ሆናለች>›ሲሉ ምሬታቸውን አሰምተዋል።

“የዓመታት የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄያችን ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም”የሚሉት የድርጅቱ ሠራተኞች፤ ባለፈው ሀሙስ  ሥራቸውን በማቆም ፦”እየራበን ነው፤ መኖር አልቻልንም!”ሲሉ ለማኔጅመንቱ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

የሳይቱ የሰው አስተዳደር ክፍል ኃላፊ አቶ አምዴ አቦነህ   ቅሬታውን አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ ግን፦ “ድርጅቱ አሁን ያለበት ሁኔታ ደመወዝ ለመጨመር የሚያስችል አይደለም”በማለት ነው ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደሌለው የነገሯቸው።

“ድርጅቱ መዋቅራዊ ጥናት በማድረግ ላይ ነው ያሉት  አቶ አምዴ፣ ‹‹ጥናቱ ወደ ማለቂያው እየተቃረበ ነው፡፡ ጥናቱ ሲያልቅ ድርጅቱ መወሰድ የሚገባውን ዕርምጃ ይወስዳል፡፡ ከዚያ በፊት  ግን ምንም ዓይነት ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ አይደለንም፤›› ብለዋል፡፡

ሠራተኞቹ ባለፈው ሐሙስ የሥራ ማቆም አድማ በማድረግ ላቀረቡት አቤቱታ፣ “ታገሱ” የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው የጠቆሙት ኃላፊው፣ “መጠበቅ አንችልም ካሉ ግን፤ ሌላ አማራጭ መፈለግ ይችላሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

ሠራተኞቹ  በበኩላቸው፦”ድርጅቱን ለቀን እንዳንሄድ እስከዛሬ የሠራንበት የአገልግሎት ክፍያ አይሰጠንም፡፡ በአሁኑ ጊዜ እኛና ቤተሰቦቻችን በልቶ ማደር አቅቶናል። የሚመለከተው የበላይ አካል  ይታደገን” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በወቅቱ ምንዛሬ መሰረት 500 የ ኢትዮጵያ ብር ፤ከ 21 ዩሮ ጋር እኩል መሆኑን፤ ዓለማቀፍ  የምንዛሬ ለውጥ መረጃ(ዩኒቨርሳል ከረንሲ ኮንቨርተር) የሚያመለክት ሲሆን፤

ይህም ማለት የ500 ብር የወር ደሞዝተኞች ፤የቀን ገቢያቸው ከ አንድ ዩሮ በታች 0.70 ዩሮ ሳንቲም ነው ማለት ነው።

“የዋጋ ግሽበቱ ጣራ በነካበት ሁኔታ ሰው እንዴት በዚህ ደመወዝ ሊኖር ይችላል?”የሚል ጥያቄ ብዙ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች እያነሱ ቢሆንም፤ ይባስ ብሎ ሠራተኞቹ ከዚሁ ደመወዛቸው ላይ ለአባይ ግድብ ቦንድ እንዲገዙ መደረጋቸው-ነገሩን በዕንቅርት ላይ ዕባጭ አድርጎታል።

በግዴታ የቦንድ ግዥ በመማረር፦“እህሉ የተዘራው ዛሬ ማታ፤ የሚደርሰው ለፍልሰታ” ማለት የጀመረው አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ ከዛሬ ሰባትና ስምንት ዓመት በሁዋላ መብራት እንድናገኝ ፤ዛሬ በረሀብ መቀጣት አለብን ወይ? ግድቡ የሚሠራው ለእኛ ነው? ወይስ እኛ ለግድቡ ግብሮች ነን? አንድ ግድብ እንዲሠራ፤ የሚሊዮኖች ህይወት በችግር መፍረስ አለበት ወይ?” እያለ በመጠየቅ ላይ ይገኛል።