(ኢሳት ዲሲ–ጥር 14/2011) የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ከመንፈቅ በፊት ተግባራዊ ያደረገው የምህረት አዋጅ ትናንት ማብቃቱ ተገለጸ።
ከ13 ሺ በላይ ሰዎች በዚህ የምህረት አዋጅ ተጠቃሚ መሆናቸውም ተመልክቷል።
ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዳስታወቀው ከሀምሌ ወር ጀምሮ ተግባራዊ በሆነው በዚህ የምህረት አዋጅ በወህኒ የሚገኙ 250 እስረኞች ሲፈቱ በሌሉበት የተፈረደባቸው 430 ዜጎችም የምህረት ሰርተፊኬት ማግኘታቸውን የጠቅላይ አቃቤ ህግ ሃላፊዎች ለመንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
2 ሺ 131 የፌደራል ፖሊስ አባላት እና 6ሺ 655 የመከላከያ ሰራዊት አባላት በምህረት አዋጁ ተተቃሚ መሆናቸውም ተገልጿል።
ምህረት ካገኙት ውስጥ 160 የሚሆኑት በኦንላይን ማመልከቻ አቅርበው ምላሽ ያገኙ መሆናቸውም ተመልክቷል።
በክልል ደረጃ ምህረት ካገኙ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት በአማራ ክልል ሲሆን፣ለ 2 ሺ 923 ሰዎች ምህረት ተደርጓል።
ትግራይ ክልል 144 ፣ደቡብ ክልል 108 ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 94 ኦሮሚያ ክልል 62 እንዲሁም ሀረሪ ክልል 50 ሰዎች በምህረት አዋጅ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል።
በምህረት አዋጁ ተጠቃሚ የሆኑት አብዛኛው በፌደራል ደረጃ ያመለከቱ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በ 6 ወራት ውስጥ ምህረት ያገኙት 13 ሺ ዜጎች ናቸው።
ይህ የምህረት አዋጅ ተጠቃሚዎች ቁጥር የሶስት ክልሎችንና የመከላከያ ሰራዊት የተወሰኑ ክፍሎችን እንዳላካተተም መረዳት ተችሏል።
የምህረት አዋጁ በዘር ማጥፋት እንዲሁም በሙስና እና መሰል ወንጀሎች የተከሰሱትን እንደማይመለከት መገለጹ ይታወሳል።
የምህረት ግዜ ገደቡ የተጠናቀቀ ቢሆንም ጥያቄ የሚያቀርቡ ወገኖች ካሉ ጉዳዩ ለመንግስት ቀርቦ ውሳኔ እንደሚሰጥበትም የጠቅላይ አቃቤ አቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ ለኢዜአ ገልጸዋል።