ኦነግ የአመራር እና የአባላቱ እስራት እንዲቆም ጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 14/2011) የኦሮሞ ነፃነት ግንባር  (ኦነግ) በአመራር እና በአባላቱ የተጀመረው እስራት እንዲቆም ጥሪ አቀረበ፡፡

ኦነግ  በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ የኦነግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ የሆኑትን አቶ ጀቢሳ ገቢሳ ጨምሮ የኦነግ አመራሮች እና አባላት አርብ ዕለት መታሰራቸውን ይፋ አድርጎል፡፡

ቀደም ብሎ ኮለኔል ገመቹ አያና እንደታሰሩበትም  አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና በመንግስት መካከል የተፈጠረውን  ውዝግብ በእርቅ ለመቋጨት የኦሮሞ አባገዳዎች ያዘጋጁት ስብሰባ በዛሬ እለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

የኦሮም አባገዳዎች  በአዲስ አበባ በጠሩት በዚህ  ጉባኤ ላይ  ኦነግ ሰራዊቱን ለአባገዳዎቹ አስረክቦ ሰላማዊ ትግሉን እንደሚቀጥል ቃል ገብቷኣል።

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በሳምንቱ መጨረሻ “ የኢትዮጵያ መንግስት  በኦሮሞ ነፃነት ግንባር አመራር አካላት እና በአባላቱ ላይ የሚካሄደው ዛቻና እስራት በአስቸኳይ እንዲቆም እንጠይቃለን፡፡ “ በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ የታሰሩ አባላቱን ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡

የኦነግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ጀቢሳ ገቢሳ፣ አቶ አማን ፍሌ፣ ዶክተር ቡሊ ኢጀታ፣ አቶ ደምቢ ተሾመ፣ አቶ ገልገሎ ዋርዪ እና አቶ ኢዶሳ ታደሰን ጨምሮ የኦነግ አመራሮች አባላት እና ደጋፊዎች በመንግስት የደህንነት ሃይላት ተይዘው ታስረዋል ብሏል፡፡

ጥር 9 ቀን 2011 ደግሞ ክሎኔል ገመቹ አያና አቶ ፈቃዱ ከተባሉ ጓደኛቸው ጋር ተይዘው መታሰራቸውን ኦነግ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በመላው ኦሮሚያ በኦነግ አባላትነት እና ደጋፊነት የተጠረጠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል ሲልም በመግለጫው አስፍሯል፡፡

የህግ የበላይነትን ለማክበር በሚል እየተወሰደ ያለው ይህ ርምጃ የተጀመረውን ለውጥ ያደናቅፋል እንጂ አይጠቅምም በማለት የሚያሳስበው ኦነግ የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል በማክበር ከኋላ ጉዞው ይገታ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

የታሰሩት  አባላቱ እና አመራሩ  እንዲፈቱ በመጨረሻ ጥሪ ያቀረበው ኦነግ የለውጡ  ችቦ እንዳይጠፋ፣ ትግሉም እንዳይቀለበስ በጋራ እነነሳ ሲልም ለኦሮሞ ህዝብ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና በመንግስት መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ለመቋጨት በኦሮሞ አባገዳዎች የተጠራው ስብሰባ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄዷል።

በአባ ገዳ በየነ ሰንበቶና በሌሎች የኦሮሞ አባገዳዎች በተጠራው እና  በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል ማዕከል በተዘጋጀው መድረክ የኦነግ መሪ አቶ ዳውድ ኢብሳ እና የኦዴፓ  ከፍተኛ አመራር ዶክተር አለሙ ስሜ ተገኝተዋል፡፡

ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት በዚህ መድረክ  ኦነግ ሰራዊቱንና ትጥቁን  ለአባገዳዎቹ አስረክቦ ሰላማዊ ትግሉን እንደሚቀጥል ቃል ገብቷል።