(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 2/2010)ለሜድሮክ ኢትዮጵያ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ፈቃድ መታደሱን በመቃወም የተካሄደውን መጠነ ሰፊ የሕዝብ እንቅስቃሴ ተከትሎ የሜድሮክ ፈቃድ መታገዱን መንግስት ይፋ አድርጓል።
የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር ትላንት እንዳስታወቀው ተጨማሪ ጥናት ተካሂዶ ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ ሜድሮክ ወርቅ የማምረት ስራውን እንዲያቋርጥ ተደርጓል ተብሏል።
ባለፉት 20 አመታት በለገደምቢ ወርቅ ሲያመርት የቆየው የሼህ መሃመድ አላሙዲን ንብረት የሆነው ሜድሮክ የወርቅ ማምረቻ በቅርቡ ለተጨማሪ 10 አመታት ወርቅ እንዲያመርት ፈቃዱ ታድሶለት ነበር።
ሆኖም የአካባቢው ሕዝብ በዚህ የወርቅ ማምረት ሒደት ስራ ላይ የዋለው ኬሚካል ያመጣውን ጉዳት በማስታወስ ለተቃውሞ አደባባይ ወጥቷል።
ወርቁን ለማውጣትና ለማጽዳት ሜድሮክ የሚጠቀምባችው ኬሚካሎች በአካባቢው በነዋሪው ላይ የጤና ችግር አስከትሏል።
በአካባቢው የሚወለዱ ሕጻናትም አካል ጉዳተኛ ሆነው እንዲወለዱ ከማድረግ ጀምሮ በአካባቢው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ነዋሪዎች ይገልጻሉ።
ባለሙያዎችን መሰረት ያደረጉ ዘገባዎችም የማህበረሰቡን ቅሬታ ትክክለኛነት አረጋግጠዋል።
በቅርቡ ለሜድሮክ ጎልድ የተጨማሪ አስር አመታት ውል መታደሱ የቀሰቀሰው ቁጣ ሕዝቡ ከሳምንት በላይ በአደባባይ ያልተቋረጠ ተቃውሞ ውስጥ እንዲቀጥል ያደረገው ሲሆን በሒደቱ ሰዎችም ተገድለዋል።
ሆኖም ሕዝቡ ተቃውሞውን ከሳምንት በላይ ያለማቋረጥ ማካሄዱን ተከትሎ የፈቃዱ መታገድ በይፋ ተገልጿል።
የማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አንድ የስራ ሃላፊ ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን ትላንት እንደገለጹት በጉዳዩ ላይ እንደገና ጥናት ተካሂዶበት ውሳኔ እስኪያገኝ የሜድሮክ ወርቅ ማምረቻ የለገደንቢ ፕሮጀክት ታግዷል።
የኦሮሚያ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባና ኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን ማሰረዙም ይታወሳል።