በቂሊንጦ ከችሎት የተመለሱ 11 እስረኞች ጨለማ ክፍል ውስጥ እንዲዘጋባቸው ተደረገ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 2/2010) በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ቃጠሎ በማስነሳት ግድያ ፈጽመዋል በሚል ክስ ከተመሰረተባቸው 30 ያህል እስረኞች አስራ አንዱ ችሎት ውለው ሲመለሱ ጨለማ ክፍል ውስጥ እንዲዘጋባቸው መደረጉ ተገለጸ።

ከትላንት በስቲያ ፍርድ ቤት ቀርበው የተከላከሉ ብይን የተላለፈባቸው እስረኞች ዛሬ ወደ ጨለማ ቤት ሲወሰዱ በነበረው ተቃውሞ በግቢው ውስጥ ውጥረት መንገሱም ተሰምቷል።

ማክሰኞ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ከቀረቡት ተከሳሾች 8ቱ በነጻ ሲሰናበቱ 30ዎቹ በተለያየ ደረጃ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል።

ከነዚህ ውስጥ አራቱ በቃጠሎው ወቅት በሞቱት ነፍስ ተጠያቂ ናቸው ሲል ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ወስኗል።

የልብ ሐኪሙ ዶክተር ፍቅሩ ማሩ እንዲሁም የኢትዮጵያ አየር ሃይል አብራሪው የመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤን ጨምሮ 26ቱ የተመሰረተባቸው የአሸባሪነት ክስ ወደ አመጽ ማደራጀት ዝቅ ብሎ እንዲከላከሉ ተወስኗል።

በእለቱ ይህ ብይን በተሰጠበት ወቅት ከተከሳሾቹ አንዱ እንዴት የገዛ ጓደኛህን ገድለሃል ተብዬ ይበይንብኛል ሲል ያሰማውን ተቃውሞ ተከትሎ በፍርድ ቤቱ አካባቢ ግርግር መፈጠሩና ከፍተኛ ዋይታም እንደነበር ተዘግቧል።

ከእለቱ ችሎት ወደ ቂሊንጦ ወህኒ ቤት የተወሰዱት እስረኞች ብይኑን በመቃወም ትላንት የረሃብ አድማ መጀመራቸው ተመልክቷል።

በቂሊንጦ ዞን 5 የሚገኙት ተከሳሾች ከችሎት መልስ መደብደባቸው ለረሃብ አድማው አስተዋጾ እንዳደረገም ተዘግቧል።

በዕለቱ ብይን ከተላለፈባቸው ከ30 ከሚበልጡ እስረኞች ውስጥ አስራ አንዱ ተነጥለው ዛሬ ወደ ጨለማ ቤት ተወስደዋል።

በዞን አንድ የሚገኙ እስረኞች ተነጥለው ወደ ጨለማ ቤት መወሰድ የለባቸውም የሚል ተቃውሞ በማሰማታቸው ግርግር መፈጠሩም ተመልክቷል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በግቢ ውስጥ የተፈጠረ የተለየ ነገር ባያኖርም አስራ አንዱ እስረኞች ግን ጨለማ ቤት እንዲገቡ ተደርገዋል።