አንዳርጋቸው ጽጌ ይፈታ በሚል የተካሄደው ዘመቻ የተሳካ ነበር ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 2/2010)ለሶስት ቀናት በማህበራዊ መድረኮች የተጠራውና አንዳርጋቸው ጽጌ ይፈታ በሚል የተደረገው ዘመቻ የተሳካ እንደነበር አስተባባሪዎቹ ገለጹ።

በሀገር ውስጥ በሚገኙ አክቲቪስቶች የተጠራው ዘመቻ በሶስት ቀናቱ ቆይታ ስለአንዳርጋቸው ጽጌ የተላለፉት መልዕክቶችና የህዝቡ ተሳትፎ ከተጠበቀው በላይ እንደሆነም ገልጸዋል።

ዘመቻው ወደፊትም በተለያዩ ፕሮግራሞች የሚቀጥል መሆኑንም አስታውቀዋል።

የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ በሰማያዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን የተመለከተ ውይይት መዘጋጀቱንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

አንዳርጋቸውን ነፃ ማውጣት ኢትዮጵያዊነትን ማክበር ነው በሚል መሪ ቃል  ለሶስት ቀናት የተካሄደው ዘመቻ ዛሬ በመዝጊያ ፕሮግራም ተጠናቋል።

በዋናነት በሀገር ቤት በሚገኙ አክቲቪስቶች የተመራው ዘመቻ በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ በሰፊው መካሄዱ ታውቋል።

በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንም ዘመቻውን የተመለከቱ ዜናዎችና ፕሮግራሞች እንዲተላለፉ በመደረጉ ከታቀደው በላይ የዘመቻው ዓላማ መሳካቱን  አስተባባሪዎቹ ለኢሳት ገልጸዋል።

በሃገር ቤት ያሉ ኢትዮጵውያን በዛ ያለውን አፈና በመቋቋምና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ሆነው ዘመቻው እንዲሳካ ማድረጋቸው አስደስቶናል ያሉት አስተባባሪዎቹ በቀጣይ አቶ አንዳርጋቸውን በተመለከተ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጉልበትና አቅም የሰጠን ዘመቻ ነው ብለዋል።

በሶስት ቀናቱ ዘመቻ አብዛኛው የማህበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የፕሮፋይል ምስልን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ፎቶግራፍ በማድረግ፣ በአንዳርጋቸው ዙሪያ እሱ የጻፋቸውንና በሌሎች የተጻፉ የተለያዩ ጽሁፎችን በማጋራት፣ በትግል ቦታ የተነሳቸውንና ከቤተሰቡ ጋር የሚታይባቸውን ፎቶግራፎች በማሰራጨትና በሌሎች ተግባራት የተከናወነው ዘመቻ አቶ አንዳርጋቸው በአስቸኳይ መፈታት እንዳለበት መልዕክት ማስተላለፍ ዋና ዓላማው በማድረግ ተጠናቋል።

ዛሬ በመዝጊያ ስነስርዓቱ የአቶ አንዳርጋቸውን ፎቶግራፍ በፌስቡክና በቲውተር ላይ በመለጠፍ ለአምስት ደቂቃ በተመሳሳይ ሰዓት በዓለም ዙሪያ አንዳርጋቸው ነጻ ይሁን የሚል መልዕክት በማሰራጨት ተከናውኗል።

ከዘመቻው አስተባባሪዎች አንዱ የሆነችው አክቲቪስት መስከረም አበራ ለኢሳት እንደገለጸችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደተነሳ በሌሎች እንቅስቃሴዎች የአንዳርጋቸውን ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ይደረጋል።

በሀገር ቤት የሚገኘው ህዝብ ከዚህም በላይ መንቀሳቀስ እንደሚፈልግ የገለጸችው አክቲቪስት መስከረም አበራ በቀጣይ በርካታ ስራዎችን ከህዝቡ ጋር በመሆን ለማከናወን እቅድ እንዳላቸውም ጠቅሳለች።

በዘመቻው ለተሳተፉትም ምስጋና አቅርባለች።

ሌላዋ የዘመቻው አስተባባሪ አክቲቪስት ኢየሩሳሌም ተስፋው ለኢሳት በሰጠችው ቃለምልልስ አንዳርጋቸውን ነጻ ማውጣት ኢትዮጵያዊነትን ማክበር መሆኑ በሚገባ የተስተጋባበት ዘመቻ ሆኖ ተጠናቋል ብላለች።

በተያያዘ ዜናም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በተመለከተ በአዲስ አበባ በሰማያዊ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ውይይት ሊደረግ መሆኑ ታውቋል።

አንዳርጋቸው ሲታወስ በሚል ርዕስ በአክቲቪስት መስከረም አበራ በሚቀርብ የመነሻ ጽሁፍ ውይይቱ የሚካሄደው የፊታችን ቅዳሜ ግንቦት አራት መሆኑንም የደረሰን መረጃ አመልክቷል።