የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት የውሳኔ ቀጠሮ ተራዘመ

በተራዘመ የፍርድ ሄደት የሚሰቃዩት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት ፣ የመጨረሻ ብይን ሚያዚያ 30 እንደሚሰጥ አስቀድሞ ቀጠሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ የብይኑ ቀን እንደገና ተራዝሟል። የመራዘሙ ዜና አስቀድሞ በኢሳትና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተዘገበ በመሆኑ፣ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አስገራሚ አላደረገውም።
አገሪቱን የሚመራት የደህንነት መስሪያ ቤት ከምርጫው በፊት ምንም አይነት ውሳኔ እንዳይሰጥ ትእዛዝ አስተላልፎአል። በተለያዩ የማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን የተቃውሞ ጽሁፎችን በመጻፍ እንዲሁም አልፎ አልፎ የስልክ ግንኙነት ማቋረጥና የሳንቲም መሰብሰብ ማእቀብ በማድረግ ሰላማዊ ትግላቸውን እያካሄዱ ያሉት ሙስሊም ኢትዮጵያውያን፣ ከውሳኔው በሁዋላ ተቃውሞ ያስነሳሉ በሚል ፍርሃት እንዲራዘም ቢደረገም፣ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ግን ንጹሃን መሪዎቻቸው እስካልተፈቱ ድረስ ትግሉ እንደማይቆም እየገለጹ ነው።
በአቶ አቡበክር አህመድ ስም በተከፈተው መዝገብ በሰፈሩት የኮሚቴው አባላት ላይ ፣ እስካሁን ድረስ በሽብር ወንጀል ሊያስከስሳቸው የሚችል ጠንካራና አሳማኝ ማስረጃ ሊቀርብባቸው አልቻለም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሚሰጠው ውሳኔ የፖለቲካ እንጅ የፍርድ ቤት ውሳኔ አለመሆኑ አንዳንድ ጠበቆች ቀድም ብለው አስተያየቶችን ሰጥተዋል።
መሪዎቹ በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ስቃይ ከደረሰባቸው በሁዋላ፣ በቴሌቪዥን ወንጀል እንደሰሩ ተደርጎ ዘጋቢ ፊልም ተሰርቶባቸዋል።
በርካታ የአዲስ አበባ ሙስሊሞች የትግል አጋርነታቸው ለመግለጽ ከሌሊት ጀምሮ ወደ ልደታ ፍርድ ተጉዘዋል።