መጋቢት ፳፬ (ሃያ አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የተከሳሽ ቃላቸውን በመስጠት ላይ ያሉት የሙስሊም የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት በፍርድ ቤቱ ውስጥ የሚያሰሙት ንግግር የብዙዎችን ታዳሚዎች ቀልብ እየሳበ መምጣቱን እና በእስረኞች ላይ የሚታየው ጽናት የሚያስገርም መሆኑን ችሎቱን የሚከታተሉ ታዳሚዎች ገልጸዋል።
ትናንት ቃላቸውን የሰጡት የኮሚቴው ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ የሙስሊሙ ኢትዮጵያዊ ትግል በዝርዝር አቅርበዋል። በእስር ቤት ውስጥ የደረሰባቸውን በደልም የታዳሚውን ስሜት በነካ መልኩ አቅርበዋል።
ኡስታዝ አህመድ ጀቢልም ዛሬ በሰጡት ቃል አሸባሪ አለመሆናቸውን፣ የፈለገ አይነት ስም ቢወጣላቸውም ለበዳዮች እንደማያጎበድዱ ገልጸዋል።
በእስር ቤት ውስጥ በሌሎች እስረኞች ላይ መስክረው እንዲወጡ የተጠየቁ ሰዎች መኖራቸውን፣ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ባልሆኑት ላይ ደግሞ ” እንስሶችም እንኳ የማይችሉት ድብደባ እንደተፈጸመባቸው” ገልጸዋል።
ታዘቢዎች እንደሚሉት በጠንካራ መንፈስ ውስጥ የሚገኙት መሪዎች፣ መንግስት በተደጋጋሚ ለሚያቀርበው የስም ማጥፋት ወንጀልም ቦታ የሰጡት አይመስልም።
መንግስት የሙስሊም መሪዎችን በማሰር የሙስሊሙን ትግል አዳክማለሁ ብሎ ቢነሳም፣ ባለፈው አርብ በአንዋር መስጊድ የታየው ተቃውሞ እንዲሁም ችሎቱን ለመከታተል ፍላጎት የሚያሳየው ህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ትግሉ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።