ታህሳስ 12 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በትግራይ ውስጥ ወታደር ለመቅጠር ተቸግረን ነበር ሲሉም ተናግረዋል።
መከላከያ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ከትናንት በስቲያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ውስጥ ለተሰበሰቡት የኢህአዴግ አባላት የመስሪያ ቤታቸውን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት -ከብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ከአቶ ግርማ ሰይፉ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሲሰጡ ነው።
ከሳምንታት በፊት በ አዲስ አበባ በተካሄደውና በአቶ መለስ ዜናዊ በተመራው የኢጋድ አባል አገራት ስብሰባ ላይ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ ከፍተኛ የ ኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣን፤ ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ሶማሊያ እንደላከች ለሮይተርስ የዜና ወኪል መግለጻቸው ይታወሳል።
እኚሁ ባለስልጣን ፤ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጦሯን የላከችው፤ ከአልሸባብ ጋር እየተፋለመ ያለውንና በከባድ ክረምት ሳቢያ ችግር ያጋጠመውን የኬንያን ጦር የኢትዮጵያ ጦር ያግዘው ዘንድ፤ ከኢጋድ ጥያቄ በመቅረቡ ነው ብለዋል።
ባለስልጣኑ የ አገራቸው ጦር ወደ ሶማሊያ መዝለቁን የተናገሩት፤ በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የ አፍሪቃ ረዳት ሴክሬታሪ ጆኒ ካርሰን፤ ኢትዮጵያ ዳግም ወደ ሶማሊያ እንዳትገባ ባስጠነቀቁ ማግስት ነበር።
ዓለማቀፍ የዜና ተቋማትም “ ሠራዊቷ ወደ ሶማሊያ ግዛት ፈጽሞ እንዳልገባ ስታስተባብል የቆየችው ኢትዮጵያ፤” ጦር መላኳን አመነች” በመሰለት በስፋት መዘገባቸው አይዘነጋም።
ከዚህም ባሻገር የዓይን እማኞችን በመጥቀስ በባይደዋ የሚገኙ የ ዓለማቀፍ ዜና ተቋማት ጋዜጠኞች ባስተላለፉት ዘገባ፤ከመቶዎች በሚበልጡ ከባድ የጦር ተሽከርካሪዎች ላይ የሰፈሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች፤ በታንክና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ታጅበው ወደ ማዕከላዊና ምዕራባዊ ሶማሊያ አምርተዋል።
ከፍተኛየተባሉት የመንግስት ባለስልጣን ጦሩ ወደ ሶማሊያ መግባቱን ባመኑና ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ይህን በዘገቡ በሳምንታት ውስጥ ነው የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፌርጌሳ እንደገና “የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያ አልገባም” በማለት የተናገሩት።
“ የመከላከያ ሚኒስትሩ ጦሩ ወደ ሶማሊያ አልገባም በማለት ዳግም ለምን ማስተባበል ፈለጉ?”በማለት ኢሳት ያነጋገራቸው አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፦ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 2006 ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ስታስገባ አቶ መለስ የጦሩ ቆይታ ለአጭር ጊዜ ነው ቢሉም ጦሩ ለዓመታት ቆይቶ ያለውጤት መመለሱን በማስታወስና – ከሳምንታት በፊትም ስማቸውን ያልገለጹ አንድ ባለስልጣን ወደ ሶማሊያ ዳግም የገባው ጦር ለአጭር ጊዜ የሚቆይ ነው በማለት ተመሳሳይ ነገር መናገራቸውን በማውሳት፦”ሆኖም ከገቡ በሁዋላ ሁኔታውን ሲያዩት እንዳሰቡት በ አጭር ጊዜ የሚጨርሱት ዘመቻ እንዳልሆነ ስለተረዱ ይሆናል “አልገባንም” በማለት ዳግም ለማስተባበል የፈለጉት” ብለዋል።
ሁለተኛው ግምቴ ደግሞ የኢህአዴግ ሹመኞች ሁሌም የሚናገሩት እውነቱን ሳይሆን አቶ መለስ ይወዱታል ብለው የሚያሰቡትን ከመሆኑ አንፃር የመከላከያ ሚኒስትሩም እንደዛ ያሉት አቶ መለስን እያሰቡ ይመስለኛል ያሉት እኚሁ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር፤ይሁንና በአቶ መለስ ለመወደድ እያሉ ከአቶ መለስ በላይ ኢህአዴግ መስለው ለመታየት የሚሞክሩ ባለስልጣናት በራሳቸው በአቶ መለስ ሲዋረዱ እንደሚታዩ ምሳሌዎችን በመጥቀስ አብራርተዋል።
የ አሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ለምን በመንግስት “ጃም” ተደረገ?” ተብለው የተጠየቁት የኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ደ ኤታው አቶ ሽመልስ ከማል መንግስት አንድንም ሬዲዮ ጃም እንዳላደረገና ዲሞክራሲያዊ ባህርይው ይህን ለማድረግ እንደማይፈቅድለት በ አደባባይ በተናገሩ ማግስት አቶ መለስ በ አደባባይ “ጃም ያደረግነው እኛ ነን” በማለት መናገራቸውን አስታውሰዋል- የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው።
እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፦”በድርቅ ምክንያት የሞተ አንድም ሰው የለም” ብለው በተናገሩ በ አጭር ጊዜ ውስጥ አቶ መለስ፦ “ የ እርዳታ እህል መድረስ የጀመረው በሱማሌ ክልል ሰው መሞት ሲጀምር ነው” ማለታቸውን ያስታወሱት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው፤ የመከላከያ ሚኒስትሩም እንደሌሎቹ ባለስልጣናት ዋሽተዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል መከላከያ ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ወታደሮችን ለመመልመል ባደረገው እንቅስቃሴ ችግር አጋጥሞት እንደነበር ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ተናግረዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊቱ ክልላዊ ተዋፅኦ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ ለውጥ እያሳየ መጥቷል ያሉት አቶ ሲራጅ፤ይሁንና የዛሬ ሁለት እና ሦስት ዓመት ገደማ በትግራይ ክልል አዲስ ምልመላ ለማካሄድ መከላከያ ሚኒስቴር ችግር ገጥሞት እንደነበር አውስተዋል። “የዛሬ ሁለት እና ሦስት ዓመት አካባቢ በትግራይ ክልል የወታደር ምልመላን በተመለከተ አመራሩ ላይ የተወሰነ የአመለካከት ችግር ነበር። የእኛ ክልል ከድሮ ጀምሮ ሰዎች ሲያሰልፍ ቆይቷል። እስከመቼ ድረስ ነው እያሰለፍን የምንቀጥለው የሚል አመለካከት ተፈጥሮ ነበር። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የሚሰለፍ ኃይል እጥረት የገጠመን ሁኔታ ነበር። ከዚያ በኋላ ይሄን ችግር ከመስተዳድሩ ጋር ቁጭ ብለን በመወያየትና በመተማመን ሁኔታው ሊለወጥ ችሏል” ሲሉ ተናግረዋል።
በ አትዮጵያ ካሉት ወደ ስድሳ የሚጠጉ ጀነራሎች ውስጥ 58 ቱ የ አቶ መለስ የቅርብ ሰዎች የሆኑ የትግራይ ተወላጆች እንደሆኑ በተደጋጋሚ በዝርዝር መዘገቡ ይታወሳል።
ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ ተመጣጣኝ የሆነ የብሄሮች የስልጣን ክፍፍል የለም በማለት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ ቋሚ መላዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ዳግላስ ለሰጡት አስተያዬት አቶ መለስ የሰጡት ምላሽ፦” ኢዴይት” የሚል እንደሆነ አይዘነጋም።