የኢሚግሬሽንና ደህንነት መስሪያቤት ሰራተኞች ፓስፖርት እና ቪዛ ጠያቂዎችን ለማስተናገድ በማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ ነው

12 ቀን 2004 /

ኢሳት ዜና:-የኢሳት ዘጋቢ እንደገለጠው ኢትዮጵያውያኑ ፓስፖርት ለማግኘት ሲሉ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰአት ጀምሮ በኢሚግሬሽን ፊት ለፊት ሰልፍ ይይዛሉ።

አብዛኞቹ ፓስፖርት ጠያቂዎች ወደ ደቡብ ሱዳን፣ ደቡብ አፍሪካና  አረብ አገራት ለስራ ፍለጋ የሚሄዱ ናቸው።

በቪዲዮ ምስል አስደግፎ በላከው መረጃ እንደገለጠው በእየለቱ የሚታየው ረጅም ሰልፍ በተሽከርካሪ ፍሰት ላይም ችግር እየፈጠረ ነው። በሱዳን ኢምባሲ አካባቢ የሚታዩት ረጃጅም ሰልፎች የአገሪቱ ህዝብ ነቅሎ ሱዳን ለመግባት የቆረጠ ያስመስለዋል ሲል አስተያየቱን አስፍሯል

በአሜሪካና አረብ አገራት ኢምባሲዎች ፊት ለፊት ረጃጅም ሰልፎችን ማየት የተቀን ተቀን ትእይንት መሆኑንም አክሎ አመልክቷል። በሌላ ዜና ደግሞ የኩዌት መንግስት ኢትዮጵያውያን ሴቶች ወደ ኩዌት በመግባት በቤት ሰራተኝነት መስራት እንዳይችሉ ውሳኔ አሳልፎአል።

‘‘አልአም-አልያዋም’’ የተባለ የኩዌት ጋዜጣ  ባሰራጨው ዘገባ፤ የሀገሪቱ መንግስት ለቤት ሰራተኝነት ወደ ኩዌት የሚሄዱትን ኢትዮጵያውያንን ላለመቀበል እንቅስቃሴዎችን የጀመረ መሆኑን አስታውቋል።

 የኩዌት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር፤  የኩዌት መንግስት ወደዚህ ውሳኔ ለመድረስ  የተገደደው፤ ኢትዮጵያኖች ሰራተኞች በቀጣሪዎቻቸው ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው በሚል መሆኑን የጋዜጣው ዘገባ ያመለክታል።

ጋዜጣው ቀደም ሲልም ከኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች ጋር በተያያዘ የተለያዩ የወንጀል ሪፖርቶች ሲወጡ የቆዩ መሆኑን በማተት፤  “ሁኔታውን ይበልጥ ያባባሰው ግን በቅርቡ አንዲት ኢትዮጵያዊት ሰራተኛ አሰሪዋን በመግደሏ ነው”ብሏል።

ጋዜጣው በዚሁ ዘገባው በቅርቡ 87 ኢትዮጵያውያን ዜጐች ነፍስ ግድያን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ክስ የተመሰረተባቸው መሆኑን  በመጥቀስ፤ አንዳንድ አሰሪዎች ከዚሁ ሥጋት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያዊያኑን ወደሃገራቸው እየመለሱ መሆናቸውንም አመልክቷል።

የወንጀሉ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሄዱ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ከኢትዮጵያ ዜጐችን የወንጀል ድርጊት በተመለከተ የራሱን ጥናት በማካሄድ ላይ ነው ተብሏል።

 ዘገባው በኩዌት በአጠቃላይ ከ55ሺ በላይ በቤት ሰራተኝነት የተሰማሩ የተለያዩ ሀገራት ዜጐች መኖራቸውን ያመለክታል።

በኩዌት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በቅርቡ ከስፍራው ለ ኢሳት ያደረሱት መረጃ እንደሚያስረዳው ግን፤ ኢትዮጵያውያኑ አልፎ አልፎ ወዳላስፈላጊ የሀይል እርምጃ እየገቡ ያሉት በ አሰሪዎቻቸው እየደረሰባቸው ባለ መረን የለቀቀ ግፍና በደል በመማረር ነው።

በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በየመንገድ ላይ ጭምር በ አሰሪዎቻቸው እየተገደሉ እንደሚገኙ የገለጹት ኢትዮጵያውያኑ፤ ይሁንና በዜጎቻቸው ላይ አንድ ነገር ሲሆን እያጋነኑ በማራገብ የሚታወቁት የአገሪቱ ሚዲያዎች፤ በ ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ስላለው ተደጋጋሚ የህይወት መጥፋት  አንድም ቃል አለመተንፈሳቸው እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።

ጉዳዩን በመከታተል  ጥበቃ ሊያደርግልንና ሊሟገትልን የሚገባው በኩዌት የ ኢትዮጵያ ኤምባሲም፤ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ በመቁጠር የራሱን ቢዝነስ እያካሄደ ይገኛል ሲሉም ኢተዮጵያውያኑ  በመንግስታቸው የተሰማቸውን ሀዘን መግለፃቸው ይታወሳል።

በሌላ ዜና ደግሞ በሺ ዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በየመን በረሀ ውስጥ ወደ አገራቸው ለመመለስ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

የአለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም እንደገለጠው ለስራ ፍለጋ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ያቀኑት ኢትዮጵያውያን ወረቀት ለማግኘት ባለመቻላቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ ተገደዋል።

ከ6 ሺ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን ከሳኡዲ አረቢያና ከጃፓን መንግስታት በተገኘ ገንዘብ ወደ አገራቸው ለመመለስ መቻሉን የገለጠው ድርጅቱ፣ ቀሪዎቹን በሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ ግን የገንዘብ እጥረት አጋጥሞታል።

ኢትዮጵያውያኑ በበሽታ፣ በእባብ በመነደፍ እየሞቱ መሆኑን ድርጅቱ ገልጧል። ባለፈው ወር ብቻ ከ30 የሚበል  ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን አክሎ ገልጧል።

የመለስ መንግስት በተደጋጋሚ ኢትዮጵያ እያደገች ነው ቢልም፣ አገሪቱን ጥለው የሚወጡ ኢትዮጵያውያን ግን በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ ነው።