ህዳር 15 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አንድነት
ፓርቲ ህዳር 14 ቀን 2004 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ የኢህአዴግ አገዛዝ ብሶት የወለደው ህዝብ እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሶ፣ ብሶት የወለደው ህዝብም አምባገነኖችን ማስወገዱ አይቀሬ ነው ብሎአል።
ፓርቲው የኢትዮጵያ አምባገነኖች ከቱኒዚያው ቤን አሊ፣ ከሊቢያው ጋዳፊ፣ ከግብጹ ሙባረክ ሊመማር አለመቻላቸውን ከጳጉሜ 3 2003 ዓም ጀምሮ የሰለማዊና ህጋዊ ፖለቲካ አራማጆችንና ነጻ ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት ከሶ ወደ ወህኒ ማውረዱን በመጥቀስ ገልጧል።
ህገ መንግስቱን አስከብራለሁ በማለት ቃለመሀላ የፈጸሙት አቶ መለስ ዜናዊ ፣ ህገ መንግስቱን በመጣስ በሽብር ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች አንድም ማስረጃ ያልቀረበበት የለም በማለት ቢናገሩም፣ አለአገባብ ከተንገላቱት መካከል አራቱን ሰዎች መለቀቃቸው ክሱ ባዶ መሆኑን ያሳያል ብሎአል።
የአምባገነንነት ዳርቻው ሰፍቶ፣ የአንድነት ሊቀመንበርና ሁለት ሊቀመናብርት እስረኞችን ለመጎብኘት ወደ ቃሊቲ ቢሄዱም ፣ እንዳይጎበኙዋቸው መከልከላቸውንም ፓርቲው ጠቅሷል። ፓርቲው ፣ ምንም እንኳን ጊዜው ዬረፈደ ቢሆንም፣ አሁንም በተሳሳተ ጎዳና መጓዡን እንዲያቆም አንድነት መክሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በበእነአንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በ”ሽብርተኝነት‘ ወንጀል ከተከሰሱት ስምንት በሀገር ውስጥ በሠላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት እና ጋዜጠኞች የክስ ቻርጅ ህዳር 14 ቀን 2004 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የተከላካይ ጠበቆች ባቀረቡት የክስ መቃወሚያና የዐቃቤ- ሕግ የተቃውሞ ውድቅ ይደረግልኝ ጥያቄ ላይ ብይን መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል። የክሱን ውሎ ከተከታተሉት ዲፕሎማቶች ያገኘነው ሙሉ ዘገባ እንደሚያመለክተው አቃቢ ህግ በተከላካይ ጠበቆች የቀረቡትን ሀሳቦች በበቂ ሁኔታ ማስረዳት አልቻለም።
”ደንበኞቼ በሽብርተኝነት፣ በሀገር ክህደትና በስለላ ወንጀሎች ነው የተከሰሱት፣ እነዚህ የወንጀል ድርጊቶች ከጥርጣሬ ውጭ በሆነ ሁኔታ በማስረጃ የሚረጋገጡ ከሆነ እስከ እድሜ ልክና ከዚያም አልፎ እስከ ሞት የሚያስቀጡ ከፍተኛ ወንጀሎች ናቸው‘ ያሉት የተከሳሽ ጠበቃ ደርበው ተመስገን ደንበኞቻችን የሕግ ደረጃዎችን ባልጠበቁ ክሶችና መረጃዎች እንዳይፈረድባቸውና እንዳይቀጡ እንሰጋለን በማለት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቆቹ የዐቃቤ ሕግ የክስ አቀራረብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ”አሸባሪ‘ ተብለው በቅርቡ ከተፈረጁት ድርጅቶች መሪዎች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ሳይኖራቸው አንድ ላይ አድርጎ መክሰሱ ሆን ብሎ በደንበኞቼ ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ ነው ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ አንዷለም አራጌ በሀገር ውስጥ በሕግ የተቋቋመ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ምክትል ፕሬዝዳንትና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ 2ተኛ ተከሳሽ ናትናኤል መኮንን የአንድነት ፓርቲ የአመራር አባል፣
5ተኛ ተከሳሽ ክንፈ ሚካኤል ደበበ በሀገር ውስጥ በህጋዊነት ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ የሌላ ፓርቲ አባል፣ እንዲሁም 7ተኛ ተከሳሽ እስክንድር ነጋ ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ ሲሆን የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለም ብለዋል፡፡
በዐቃቤ- ሕግ የክስ መዝገብ የሕግ ሁኔታዎችን አያሟላም፣ በሁሉም ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ- ሕግ ያቀረበው 1ኛው ክስ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁን አንቀጽ 3/ ከንዑስ አንቀጽ1 እስከ 4 የጠቀሰ ሲሆን እነዚህ አንቀጾች በሽብርተኝነት ተግባር ሰው መግደልን፣ የሕብረተሰብ ደህንነትን አደጋ ላይ መጣልን፣ እገታና ጠለፋን እና በሽብርተኝነት ተግባር በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስን ይመለከታሉ በማለት የገለጹት የተከሳሽ
ጠበቆች፣ ነገር ግን ማን ሞተ፣ ማን ተጠለፈ፣ በንብረት ላይ ምን ጉዳት ደረሰ፣ ከተከሳሽ ደንበኞቻችን መካከል ማን የትኛውን ተግባር ፈጸመ የሚሉት በዐቃቤ- ሕግ ክስ ላይ የተብራሩ ጥያቄዎች አይደሉም ስለዚህ ክሱ
እንዲታጠፍ አሊያም በግልጽ እንዲቀመጥ ጠይቀዋል።
በሌላም በኩል 4ተኛው ክሥ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 248/ለ-ን መሠረት ያደረገ ና ከፍ ያለ የሀገር መክዳት ወንጀልን የሚመለከት ነው፣ በዚህ ክስ ዝርዝር ውስጥ በሀገር ውስጥ ለአሸባሪ ድርጅት አባል በመመልመል ወደ ኤርትራ መላክ የሚል ቢገኝበትም፣ በማን አማካኝነት እነማን ተመልምለው ሥልጠና እንደወሰዱ አይገልጽም ያሉት የተከሳሽ ጠበቆች በሀገሪቱ ሕግ ያልተከለከሉ እንዲያውም በህግ የተፈቀዱ በክሱ ላይ እንደወንጀል መቅረቡን አመልክተዋል፡፡
በወንጀል ሕግ አንቀጽ 68/ሐ መሠረት በሕግ እውቅና የተሰጠውን የግል መብት ሥራ ላይ ለማዋል የተፈጸመው ድርጊቶች አፈፃጸማቸው ከሕግ ወሰን እስካላለፉ ድረስ እንደወንጀል የማይቆጠሩና የማያስቀጡ ሆናቸው ዐቃቤ ሕግ የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን እንደ ክስ ማቅረቡ አግባብ አይደለም ሲሉ የተከሳሽ ጠበቆች ለችሎቱ አቅርበዋል፡፡
ዐቃቤ- ሕግ በበኩሉ የመጀመሪያው መቃወሚያ ክሱ ተነጣጥሎ ይቅረብልኝ የሚለው በሥነ-ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 117 ንዑስ አንቀጽ 2 እና 3 ላይ በተለያዩ ወንጀሎች በአንድ ክሥ ሊቀርብ እንደሚችል ያሳያል፣ ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ተቃውሞውን ውድቅ ያድርግልኝ ብሏል፡፡
ወንጀሉ የተፈጸመበት ቦታና ጊዜ አልተጠቀሰም የሚለው የተከሳሽ ጠበቆች የመቃወሚያ ነጥብ ላይ ተቃውሞ አለኝ ያለው ዐቃቤ-ሕግ፣ ” በእያንዳንዱ ተከሳሽ ግለሰብ የወንጀል ተሳትፎ ላይ ከ2001 ዓ.ም፣
ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ እያልን ጠቅሰናል፣ በዚህም ላይ እኛ እነዚህን ሰዎች አሲረዋል፣ አቅደዋል እንጂ ሰው ገድለዋል ብለን አይደለም በክሥ ዝርዝራችን ላይ ያቀረብነው፤ በነፃ የመደራጀትና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት እንደሽፋን ነው የተጠቀሙበት” ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ተቃውሞውን ሁሉ ውድቅ ያድርግልን በማለት የፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የተከላካይ ጠበቆችን መቃወሚያ እና የዐቃቤ- ሕግን ተቃውሞው ውድቅ ይደረግልኝ ጥያቄ ካደመጠ በኋላ በክሥ ቻርጁ ላይ ብይን የሰጠ ሲሆን፣ የተከላካይ ጠበቆች ካቀረቡት የተቃውሞ ጥያቄዎች ውስጥ በተከሳሾቹ ላይ በዐቃቤ- ሕግ ከቀረቡት ክሶች መካከል 1ኛው ክሥ ” የጸረ ሽብርተኝነት አዋጁን አንቀጽ 3/ከንዑስ አንቀጽ1 እስከ 4 በመጣስ ሰው መግደልን፣ የሕብረተሰብ ደህንነትን አደጋ ላይ መጣልን፣ እገታና ጠለፋንና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ የሚሉ የክስ ፍሬ-ሃሳቦችን ” እና 4ተኛው ክሥ ከፍተኛ የሀገር ክህደት የሚለውን የክሥ ፍሬ-ሃሳብ ተብራርተውና ተስተካክለው በግልጽ
እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡
በሌላ በኩል የተከላካይ ጠበቆች ባቀረቡት መቃወሚያ ላይ “ያካተቷቸው የክስ ሂደቱ በአሸባሪነት ከተፈረጁት የግንቦት 7 የአመራር አባላት ጋር ተለይቶ መታየት አለበት፣ በዐቃቤ- ሕግ የክሥ ዝርዝር ላይ ወንጀሉ
ተፈጸመበት የተባለው ጊዜና ቦታ አልተጠቀሰም፣ የክሥ አቀራረቡ የሕግ ሁኔታዎችን አያሟላም የሚሉ ነጥቦችን ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎት” ለህዳር 20 ቀን 2004 ዓ.ም ተለዋጭ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ሰረኞቹ የመጎሳቆል ምልክት እንደሚታይባቸው የእስር ቤት አያያዛቸው ጥሩ አለመሆኑን ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ያገኘው መረጃ ያሳያል።