የመንግስት ጋዜጠኞች የሙስና ጥያቄ እንዳማረራቸው  ባለስልጣናት ለመንግስት ኮሚኒኬሺን ጉዳዩች አቤት አሉ፡

ኀዳር (ስምንት) ቀን ፳፻፯ / ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ ፣ በደቡብ እና  በአማራ ክልሎች በተካሄደ የመረጃ አመራር ስልጠና ላይ አሰተያየት የሰጡ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ጋዜጠኞች ‹‹ቡጨ›› በማለት የሚጠሩት  ቡጨቃ ፤ቆረጣ ወይም ሃብትን መካፈል የሚባለው አሰራር  እንዳማረራቸው ገልጸዋል።

ባለስልጣኖቹ “መንግስት ከከፈላቸው አበል ውጭ በድጋሜ አበል ካልተከፈላቸው ፕሮግራሞቻችን በደንብ አይሸፈኑም፤ ምንም አይነት ሂሳብ ካላገኙ ወይም የምግብ ፤ የነዳጅ እና ሌሎች ወጭዎች በጥሬ ብር ካልተሸፈነላቸው ስራዎችን አያቀርቧቸውም” በማለት ያማረሩ ሲሆን፣ ተገደው እንዲያቀርቡ ቢደረግም እንኳ

ከአጫጭር ዜና ያለፈ ሊሆኑ አልቻሉም ሲሉ አማረዋል። የኢቲቪን ዜና ለማግኘት በትንሹ ለጋዜጠኛው ፤ለካሜራ ባለሙያውና እና ለአሸከርካሪው ከ3000 ብር በላይ ወጭ ማዘጋጀት ግዴታ ሁኖብናል ሲሉ ባለስልጣኖቹ ለክልል የመንግስት ኮሚኒኬሺን ጉዳዩች ጽ/ቤት ሃላፊዎች አቅርበዋል፡፡

የጽ/ቤት ሃላፊዎች በበኩላቸው እኛንም ሳይቀር ያሰቅቁናል ፤ አሁን ኢቲቪን ከምንጠራ ቢቀር ይሻላል እያልንት ትተነዋል በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡ ኢቲቪ ይህን ተከትሎ ባካሄደው የሰራተኞች ግለሂስ ፣ እስከ 12 ሺ ብር ለአንድ ዘገባ እንደተቀበሉ የሚያሳይ መረጃ ቀርቧል።

በአማራ ክልል ጋዜጠኞች በሚፈፀም የድጋሜ አበል መጠየቅ ምክንያት ለጋዜጠኖች የሚሰጠው መደለያ ለክልል ም/ቤት በመቅረቡ በተካሄደ ማጣራት 16 ጋዜጠኞች ተቀጥተዋል። በደቡብ እና ኦሮምያ ችግሩ የተለመደ እንደሆነ እና የተሻለ ዘገባ ለማግኝት ብር መክፈል አሰፈላጊ መሆኑን አምነው ተቀብለው በመደለያ

እተሰራ እንደሆነ ተገልፆል፡፡ አብዛኞቹ የመንግስት ባለስልጣናት ስራዎቻቸውን በኢቲቪ ካላቀረቡ፣ እንደሰሩ ስለማይቆጠርላቸው የኢቲቪን ዘገባ እንደ ስራ ውጤት ማሳያ ይጠቀሙበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢሳት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች በጥራት እየታየ መሆኑን ዘጋቢያችን የዲሽ ተከላ ባለሙያዎችን በማነጋገር ዘግቧል።

ከህዝቡ የሚቀርበው የመጀመሪያ ጥያቄ ኢሳትን ታሳዩናላችሁ ወይ የሚል ነው የሚሉት የዲሽ ባለሙያዎች፣ ኢሳትን እናሳያለን የሚሉ ማስታወቂያዎች አደጋ የሚያመጡ ቢሆንም፣ ለገቢያችን ስንል እንለጥፋለን በማለት መናገራቸውን ዘጋቢያችን አክሎ ገልጿል።

ኢሳት ካለፉት አራት አመታት ጀምሮ በከፍተኛ ውጣ ውረድ ስርጭቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማቅረብ ላይ ይገኛል።ከ7 ጊዜ በላይ በገዢው ፓርቲ ተጽእኖ ከአየር ላይ እንዲወርድ ከተደረገ በሁዋላ፣ የተለያዩ የአሰራር ዘዴዎችን በመጠቀም ካለፉት 2 አመታት ጀምሮ ስርጭቱ ያለችግር እየተላለፈ ነው።

አድማጮች የፕሮግራም መደገጋምና ፕሮግራሞች በተያዘላቸው ሰአት አይቀርቡም በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ቢያቀርቡም፣ ድርጅቱ ባለው የሰው አቅም፣ ተመጣጣኝ አገልግሎት ለመስጠት እየሞከረ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልጻል።