የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚ/ር በትላንትናው ዕለት በሒልተን ሆቴል ድንገት በጠራው የእራት ግብዣ አዲሱ ሚኒስትርን ከጋዜጠኞችና የኮምኒኬሽን ባለሙያዎች ጋር አስተዋወቀ፡፡

ነሃሴ ፳፱(ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቅርቡ አቶ በረከት ስምኦንን በመተካት በሚኒስትርነት ወደ ጽ/ቤቱ የመጡት አቶ ሬድዋን ሁሴንን ያስተዋወቁት አቶ ሽመልስ ከማል ሲሆኑ ሰውየው ከሚዲያ ጋር ባላቸው ቅርበት፣በአንደበተ ርዕቱነታቸው፣በፖለቲካ ዕውቀታቸው የላቁ መሆናቸውን ለጋዜጠኞች በመንገር አስተዋውቀዋቸዋል፡፡

ከሳምንት በፊት ከዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዳይሬክተርነት ተነስተው በመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት በሚኒስትር ዴኤታነት ማዕረግ የተሾሙት አቶ እውነቱ ደበላም በተመሳሳይ መንገድ ተዋውቀዋል፡፡ አቶ እውነቱ ወደ ዱር እንስሳ ዳይሬክተርነት ከመዛወራቸው በፊት የፌደራል ጉዳዮች ባለስልጣን፣ ቀደም ብሎ ደግሞ የኦሮምያ ክልል የደህንነት ክፍል ሀላፊ ሆነው ሰርተዋል።

አቶ እውነቱ ከአንድ ዓመት በፊት በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በሃላፊነት በሚሰሩበት  ወቅት ከሙስሊሙ ጋር በተያያዘ በነራቸው የከረረ አቋም ይታወቃሉ፡፡

አቶ ሬድዋን ጽ/ቤቱ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ከመግለጽ ባለፈ አዲስ ዕቅድ ያላቸው ስለመሆኑ ያሉት ነገር የለም፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የመንግስትና የግል ሚዲያ መሪዎች፣ጋዜጠኞች፣የፌዴራልና የክልል መ/ቤቶች የኮምኒኬሽን ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

አቶ በረከት ስምኦን የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤትን በደቡብ አፍሪካ አቻ መ/ቤት ሞዴል አስጠንተው ስራ ከጀመሩ በሃላ በየሳምንቱ ዓርብ ለጋዜጠኞች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ከመስጠት ጀምሮ በየስድስት ወሩ የጠ/ሚኒስትሩን ከጋዜጠኞች ጋር በማገናኘት ለመስራት ሙከራ ያደረጉ ቢሆንም በተለይ የመ/ቤቱ አንድ ሚኒስትር ዴኤታ ከአገር ከኮበለሉ በህዋላ ይህ ጅምር ብዙም ሳይራመድ እንዲቆም መደረጉ ይታወሳል።

 

ኢህአዴግ በአገሪቱ ያሉ የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን ከግንባሩ መሪዎች በሚተላለፍ ወርሀዊ መመሪያ መሰረት ስራቸውን የሚሰሩበትን አዲስ አሰራር ቀይሷል።