የአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ገጠመው፡፡

ነሃሴ ፳፱(ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የዩኒቨርስቲው የማስፋፊያ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መንግሥት በተመደበ 859 ሚሊዮን 514 ሺ 332 ብር ከ42 ሳንቲም በ‹‹CDS consultancy›› ድርጅት አማካሪነት እና በሌሎች 15 ተቋራጮች ከ2001 ዓ/ም እስከ 2003 ዓ/ም ባሉት ጊዚያት  ተጀምሮ በመካሄድ ላይ ነው።

አጠቃላይ ፕሮጀክቶቹን ለማጠናቀቅ የተያዘው የጊዜ ሠሌዳ ዝቅተኛው 2 ወር ከ15 ቀናት ከፍተኛው ደግሞ 49 ወራት ነው፡፡ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ እየተከናወኑ ከሚገኙ 15 የተለያዩ ግንባታዎች መካከል እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2005 ዓ/ም የሁለት ፕሮጀክቶች  የፊዚካል አፈጻጸም ከ 43  እስከ  45 በመቶ ከደርሰ በኋላ በመቆሙ  ዩኒቨርስቲው በጥሬ ገንዘብ 445 ሚሊየን ብር ለኪሳራ እንዲዳረግ መደረጉን የውስጥ ምንጮች ገልጸዋል።

በአሁኑ ስዓት የተቌረጡት ፕሮጀክቶች የሚገኙበት ደረጃ ተገምግሞና በንብረቶች ላይ ቆጠራ ተደርጎ አዲስ ጨረታ በፋካሊቲው ባለቤትነት ለማውጣት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ ይህም አዲስ ጫራታ ዩኒቨርስቲው አስቀድሞ በእቅድ ያልያዘው ተጨማሪ 500 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ወጭ እንደሚጠይቀው ታውቋል፡፡

በዩኒቨርስቲው የተያዙት ሌሎች ፕሮጀክቶችም ከመጠናቀቂያ ጊዚያቸው እንደዘገዩ መረጃው ያመለክታል። የግንባታ ዕቃዎች እጥረት፣ ፣ አንዳንድ ኮንትራክተሮች የተሰጣቸውን ሥራ በወቅቱ አለማከናዎናቸውን ተከትሎ የተወሰደ እርምጃ አለመኖር ፣ የአንዳንድ ፕሮጀክቶች የማጠናቀቂያ  ወጪ መጨመር እና የክፍያ መዘግየት የፕሮጀክቶችን እድሜ እንዳራዘመ ዩኒቨርስቲው ይገልጻል።

በመላው ኢትዩጵያ የሚገኙ ኮሌጆች እና የዩኒቨርሲቲ ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ጥራት ከሌለው የጫራታ ስርዓት ጋር በተገናኝ በብዙ ሚሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ እንደሚያባክኑ በጄኔራል ኦዲተር መስሪያ ቤት የተሰራ ጥናት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስፋፊያ ግንባታዎች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ ሙስና እየተፈጸመ መሆኑን የውስጥ ምንጮች ይገልጻሉ። ጸረ ሙስና ኮሚሽን በዩኒቨርስቲው ላይ የጀመረው ምርመራ ይኑር አይኑር ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። በጉዳዩ ዙሪያ የዩኒቨርስቲውን ባለስልጣናት ለማናገር ያደረግነው ሙከራም እንዲሁ አልተሳካም።

የግንባታው ዘርፍ አደጋ ውስጥ መዘፈቁን እና ለጥቂት ባለስልጣናት እና አንዳንድ ነጋዴዎች መክበሪያ መሆኑን የኢህአዴግ ልሳን የሆነው ዘመን መጽሄት በቅርቡ ዘግባለች።