(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 11 /2010) መንግስት እያሳየ ያለው ከመጠን ያለፈ ትዕግስት ለሀገሪቱ አንድነትና ለዜጎች ደህንነት አደጋ መደቀኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስተያን ዛሬ ገለጸች።
በቅርብ ግዜያት ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶች ዘጠኝ አብያተ ክርስትያናት ሲወድሙ አምስት ካህናት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውንም ቤተክርስትያኒቱ አስታውቃለች ።
በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ እንዲሁም በጣና በለስ በተለይም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ያለውን ሁኔታ ትኩረት ሰጥታ የተመለከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በሰው፣ በአብያተ ክርስትያናትና በንብረት ላይ የደረሰ ጥቃቶችና ዘረፋዎች ዘርዝራለች።
በፓትሪያሪክ አቡነ ማቲያስ በተነበበው የቤተክርስተያኒቱ መግለጫ 9 አብያተ ክርስትያናት ከነሙሉ ንብረታቸው መውደማቸውን፣ አምስት ካህናት በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ ፣ሰባት ካህናት ደግሞ በደረሰባቸው ከፍተኛ ጥቃት በሆስፒታል የሚገኙ መሆናቸው ተገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ በርካታ ምዕመናን መጎዳታቸውን ንብረቶች መውደማቸውንና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስተያን ውጪ ያሉ ክርስትያኖች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት መፈጸሙን ፓትሪያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ዘርዝረዋል ።
መንግስት ለሃገራዊ መግባባት ሲል የሚያሳየው ከልክ ያለፈ ትዕግስት የሐገሪቱን አንድነት እንዲሁም የዜጎችን ደህነት አደጋ ላይ መጣሉንም መግለጫው ዘርዝሯል።
በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መንግስት በእለቱ ሕግና ስርዓት ለማስከበር የሚያደረገውን እንቅስቃሴ የትግራይ ክልል ህገወጥ ነው በማለት ሲቃወም፣ የህወሃት ደጋፊዎች፣ አባላትና የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት በተለይም የትግራይ ተወላጆች የሆኑ የሰራዊቱ አዛዦች ሕግን በማስከበሩ ሂደት እንዳይሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወቃል።