የመንግስት ባለስልጣናት እያስፈራሩዋቸው መሆኑን በፍኖተሰላም ከተማ ሜዳ ላይ ወድቀው የሚገኙት ተፈናቃዮች ተናገሩ

መጋቢት ፳  (ሃያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 

ኢሳት ዜና:-ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ተፈናቅለው በምእራብ ጎጃም ዞን በፍኖተሰላም ከተማ ሜዳ ላይ ወድቀው የሚገኙት አማራ ተወላጅ አርሶደአሮች ከክልሉ ዋና ከተማ እና ከዞኑ የተውጣጡ ባለስልጣናት ዛሬ ሰብስበው ያነጋገሩን ቢሆንም ፣ ተስፋ የሚያስቆርጥ መልስ ሰጥተውናል በማለት ለኢሳት ተናግረዋል።

አርሶአደሮቹ እንደሚሉት ባለስልጣናቱ ከተማውን ለቀው ወደ ወረዳቸው እንዲሄዱ፣ የተቀሙትን ሀብትና ንብረት በተመለከተ ጥያቄ ሲያቀርቡም ” ቀድሞ ማን ሂዱ አላችሁ አናውቅም” ብለው እንደመለሱላቸው ተናግረዋል።

ያለምንም መጠለያ 2 ሺ አባወራ ሜዳ ላይ ተጥሎ እንደሚገኝ የተናገሩት ተፈናቃዮች፣ ከንጽህና ጉድለት ጋር በተያያዘ በሽታ ተነስቶ ህጻናትና ሴቶች ሊያልቁ ይችላሉ በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል። ተፈናቃዮች ምግብ እየቀረበላቸው መሆኑን ተናግረዋል፣ ምግቡን የሚያቀርብላቸው ግን ቀይ መስቀል ይሁን መንግስት አላወቁም።

አንዲት እናት በወለደችበት እለት አካባቢውን ለቃ እንድትወጣ መደረጉን ተፈናቃዮች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ  አሁንም የቤንሻንጉል ጉሙዝን ክልል ለቀው ባልወጡ አርሶአደሮች ላይ የሚፈጸመው ግድያና እንግልት መጨመሩን በከማሼ ዞን የሚኖሩ ለመፈናቀል ተራቸውን በመጠባበቅ ላይ ያሉ አርሶአደሮች ገልጸዋል።

የተፈናቃዮችን ሀብት ለመዝረፍ በሚደረግ ሙከራ ዛሬ አንድ ግለሰብ በጥይት ተመትቶ መሞቱን ሌሎች ሁለት ሰዎች ደግሞ የደረሱበት አለመታወቁን አርሶደሮች ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ”  ለዜጎች መሞት፣ መፈናቀልና መሰደድ ተጠያቂው መንግስት ነው!!! ወንጀለኞች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን ” በሚል ርእስ ዛሬ መግለጫ አውጥቷል።

ፓርቲው በመግለጫው ” አምባገነኑ የኢህአዴግ መንግስት የሚከተለው ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝምና የስርዓቱ አራማጆች ካላቸው የስልጣን እድሜን የማራዘም ጉጉት ተደማምረው ለሃገራችን እንዲሁም ተቻችሎ፣ ተዋልዶ፣ ተዛምዶና ተዋድዶ ለዘመናት ይኖር ለነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅና አስፈሪ አደጋ ወደ መሆን እንደደረሱ በግላጭ እየታየ ነው፡፡” ብሎአል።

በማያያዝም ” ያ ለዘመናት አብሮን የቆየው በጋራ የመኖር ዕሴት እየተደመሰሰ በምትኩ የሚያጋጩ ስልቶች እየተፈጠሩና እየተተገበሩ ወደ ሰቆቃ ተለውጠው ይገኛሉ፡፡ የዜጎች ሰላዋዊና ህጋዊ መብት እየተጣሰም ነው፡፡ በኢትዮጵያችን ውስጥ አብሮ የመኖር፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና በፈለጉት ቦታ ሃብት የማፍራት ህልውና እያከተመ መጥቷል፡፡ ለዚህ ክፉ ድርጊት ተጠያቂ የሚሆነው ደግሞ የዜጎችን መዘዋወር መብትና ሃብት የማፍራት መብት ማረጋገጥ የተሳነው መንግስትና መንግስት ብቻ ነው፡፡” ብሎአል።

” ከቤኒሻንጉል ክልል የአማራ ተወላጅ የሆኑትን ዜጎች የዘመናችን ሹመኞች ከኢ-ሰብዓዊነት ባፈነገጠ መልኩ ከእቃ ለሚሰጥ ክብር ባነሰ ሁኔታ ንብረታቸውን ሳይሰበስቡ በጅምላ እየተጫኑ መጣላቸውን ቀጥለዋል፣  የሚለው አንድነት ” በርካታ ህፃናትም የዚህ ግፍ ሰለባ ሆነዋል፤ እየታፈኑ የሚሞቱትም ቁጥራቸው በርካታ” ብሎአል።

ፓርቲው በመቀጠልም “በጣም የሚያሳቅቀው ደግሞ የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑት 59 ሰዎች ሞት ጉዳይ ነው፡፡ ካላግባብ በጭካኔ  ለብዙ ዓመታት ከኖሩበት፣ ከወለዱበትና ከከበዱበት ስፍራ ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በአንድ መኪና እየታጨቁ እንዲወጡ በማድረግ ገደል ውስጥ ገብተው እንዲሞቱ የተፈረደባቸው ዜጎችን ህይወት እንዲቀጠፍ ያደረገውም በቸልታ እየገዛ ያለው የኢህአዴግ መንግስት ነው፡፡ መንግስት በነዚህ ዜጎች ላይ ለደረሰው ኢ- ሰብዓዊ ድርጊትና ህይወት ማጣት ተጠያቂ ነው” በማለት ፓርቲያችን ያምናል ብሎአል።

“ለውጭ ዜጎች እንዲበለፅጉበት በትንሽ ሳንቲም፤ ግልፅነት በጎደለውና በሙስና በተተበተበ አሰራር ለቻይና ኩባንያዎች፣ ለህንድ ኩባንያዎች፣ ለሳዑዲ አረቢያ ኩባንያዎች ወዘተ ለዜጎቻቸው ቀለብ እንዲያመርቱበት በገመድ እየተለካ የሚሰጠው የአዲስ አበባን ስፋት አምስት ጊዜ የሚበልጥ መሬት እንዴት ለዜጎቹ ይነፈጋል? ለምንስ ኢትዮጵያውያን ተዘዋውረው በኩርማን መሬት ላይ ሃብት የማፍራት መብታቸውን ተነፈጉ? ይህንን ኢሰብኣዊነት ዓለማቀፉ ማህበረሰብ፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና ኢትዮጵያውያን ሁሉ እንዲያውቁት እንፈልጋለን፡፡” ብሎአል አንድነት በመግለጫው።

ኢህአዴግንንና በእሱ የሚመራውን መንግስት ታሪክና ሕዝብ ይፋረደዋል፡፡ ይህንንም በደል እያዩና እየሰሙ ዝም ማለት የወንጀሉ ተባባሪ መሆን ማለት ነው፡፡ ዛሬውኑ ተቃውሞአችንን፣ ጩኸታችንን እናሰማ፤ በደል ሰቆቃ በቃ እንላለን፡” በማለት ጥያቄ የሚያቀርበው አንድነት፣ ለዚህ ሁሉ አገራዊ ቀውስ ተጠያቂው መንግስት መሆኑን” ገልጾ፣  ዜጎች እንዲሞቱ፣ እንዲጎሳቆሉና እንዲሰደዱ ያደረጉ ወንጀለኞች በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ የሴቶችና ህፃናት መብት እንዲከበር፣ ማፈናቀሉ አሁኑኑ እንዲቆም፣ ተጎጅዎችም ካሳ እንዲከፈላቸው እንጠይቃለን፡ በማለት አቋሙን አንጸባርቋል።

የአማራ ክልል ባለስልጣናት እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ ወይም ማብራሪያ አልሰጡም።