(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 10/2010) የመንግስት ሹማምንት ለስራና ለህክምና ወደ ውጭ በሄዱበት ሀገር የተጠቀሙበትን ገንዘብ እንደማያወራርዱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
ገንዘቡ ስለማይወራረድም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የኦዲት ጉድለት እንዳለበት አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ችግሩ ስላሳሰባቸው ጉዳዩን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል ተብሏል።
የዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ያልተወራረዱ እና መከፈል ያለባቸው ሒሳቦች እንዳሉ ቢያሳውቅም መጠኑ ግን ይፋ አልተደረገም።
እናም የመንግስት ሹማምንት ለውጭ ሀገር ህክምና እና ለስራ በሄዱበት ሀገር የተጠቀሙበትን ዕዳ በአግባቡ ሊያወራርዱልኝ ባለመቻላቸው በኦዲት ግኝት ተጠያቂ እየሆንኩ ነው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሕዥብ ተወካዮች ምክር ቤት ገልጿል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመንግስት የሀላፊነት ቦታ ላይ የተቀመጡ አመራሮች ወደ ውጭ ሀገራት በሚሄዱበት መወራረድ የሚገባውን ሂሳብ በወቅቱ እየከፈሉ አይደለም ብሏል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ9 ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ያቀረቡት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ለጉዳዩ በተደጋጋሚ መፍትሄ እንዲሰጠው ጥያቄ ቢቀርብም እስካሁን ግን የተስተካከለ ነገር የለም ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም ማስተካከያ እንዲደረግ የሚመለከታቸው አካላት መፍትሄ ሊሰጡት ይገባል ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዲፕሎማቶችና የአምባሳደሮች ምደባ ፍትሃዊ አይደለም በሚል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በም/ቤቱ አባላት ጥያቄ ተነስቷል፡፡
በተለያየ የመንግስት ሀላፊነቶች ላይ አገልግለው ለአምባሳደርነት የሚሾሙ ሀላፊዎች ላይ ግልፅ የሆነ አሰራር የለም አድሎአዊነት አለው የሚል ጥያቄ ቀርቦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በአሰራሩ ላይ የሚታየውን ችግር ለማስተካከል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአሁን በኋላ ትኩረት አድርጎ ይሰራል የተነሳውም ጥያቄ ተገቢ ነው ማስተካከያም ይደረግበታል ሲሉ ዶክተር ወርቅነህ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡