የመለስ መንግስት በመሬት ሽያጭ ፖሊሲው ተደጋጋሚ ነቀፌታ ቢደርስበትም ፖሊሲውን ለመቀየር ፍላጎት አላሳያም ተባለ

መጋቢት ፳፰ (ሃይ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መንግሰት በአገር ዉስጥና በዉጭ የሰላ ተቃዉሞ ቢሰነዘርበትም በኢትዮጵያ አነስተኛ ድሃ ገበሬዎችን ከአያት ቅድመ አያት ይዞታቸዉ ያለፈቃዳቸዉ እያፈናቀለ መሬታቸዉን ለዉጭ ከበርቴዎች የሚያከራየዉ እጅግ አነስተኛ በሆነ አመታዊ የኪራይ ዋጋ ክፍያ እንደሆነ ሮይተርስ ገለፀ።

ሮይተርስ የዜና ወኪል ይህንን ያስታወቀዉ አነስተኛ ክፍያዉን ከፍ ለማድረግ አስፈላጊ የመሰረተ ልማት አዉታሮችን ለመዘርጋት እቅድ እንዳለዉ በግብርና ሚኒስቴር የኢንቬስትሜንት ባለስልጣን ሃላፊ የሆኑት አቶ ኢሳያስ ከበደ የሰጡትን መግለጫ መሰረት በማድረግ ነዉ።

የመለስ መንግስት  በእርሻ ስራ ላይ ለሚሰማሩና ምርታቸዉን ለዉጭ ገበያ ለሚያቀርቡ የዉጭ አገር ከበርቴዎችና ባለሃብቶች 3.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በርካሽ አመታዊ የኪራይ ዋጋ ለማከራየት መመደቡ የሚታወስ ሲሆን ካራቱሪ ግሎባልና ሳዉዲ ስታር የመሳሰሉ በርካታ ድርጅቶች መሬት ተረክበዉ ስራ የጀመሩ መሆኑ ይታወቃል።

የግብርና ሚኒስቴር ድረ ገፅ እንደሚያሳየዉ ድሃዉ ገበሬ ከመተዳደሪያ ርስቱ ባለቤትነት በህገ ወጥ መንገድ እየተፈናቀለ መሬቱ ለዉጭ ከበርቴዎች በመሰጠት ላይ ያለዉ በሄክታር ከ12.8 – 1.15 የአሜሪካን ዶላር ወይንም ( ከብር 256.00 – ብር 23.00 ) ለሚሆን እጅግ ርካሽ አመታዊ የኪራይ ገቢ መሆኑ ተጠቅሷል። 

ይህንኑ የእርሻ መሬቶቹ በሄክታር በርካሽ የሚቸበቸቡበትን አመታዊ የኪራይ መጠን ለማሳደግ መንግስት  በአካባቢዎቹ መንገድ፤ የስልክና የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋት ሌላ እቅድ ማዉጣቱን ባለስልጣኑ አስረድተዋል። 

እንደባለስልጣኑ አባባል ኩባንያዎቹ የመሬት ኪራዩን የወሰዱት ከ20 – 40 አመት ለሚሆን ጊዜ ቢሆንም መንግስት የሚያከናዉናቸዉ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንደተጠናቀቁ የኮንትራቱ ጊዜ እንደሚያጥርና ክፍያዉም እንደሚጨምር ለሮይተርስ ገልፀዋል። መንግስት የሚላቸዉ የመሰረተ ልማቶች ግንባታ የሚጠናቀቅበትን ጊዜ ባለስልጣኑ ከመግለፅ ተቆጥበዋል።

የመለስ መንግሰት ባለስልጣን የሰጡትን ይህን መግለጫ በተመለከተ አስተያየታቸዉን እንዲሰጡ ኢሣት ያነጋገራቸዉ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ በሰጡት አስተያየት፤ ” ከህግ ዉጭ እጅግ አነስተኛ በሆነ አመታዊ የኪራይ ዋጋ አነስተኛ ድሃ ገበሬዎችን ከይዞታቸዉ ለማፈናቀል የወሰደዉ እርምጃ በምንም መልኩ ተቀባይነት ባለማግኘቱ በያቅጣጫዉ ከሚሰነዘርበት የሰላ ሂስ ለማምለጥ የሚያደርገዉ መዘላበድ ነዉ። ቀድሞዉንስ በምን ላይ ተመርኩዞ ነዉ ያን ያህል ርካሽ አመታዊ የኪራይ ዋጋ ለመተመን የቻለዉ? ለምን ቀድሞዉኑ አልታሰበበትም፤ ወይንም ለምን በብዙ አገሮች እንደተለመደዉ ሁሉ ኢንቬስተሮቹ እነዚህን የመሰረተ ልማቶች እንዲዘረጉ በዉለታዉ ዉስጥ እንዲካተት አልተደረገም? ሃሳቡ ለአዳዲስ የመሬት ተዋዋዮች ከሆነ ምናልባት ሊሰራ ይችል ይሆናል። ዉለታ ለፈፀሙት ግን እንዴት ሊሰራ ይችላል? ከመሰራቱ በፊት ስምምነት ሊጠየቁ አይገባም? ከ20 – 40 አመታት ለሚሆን ጊዜ ኮንትራት የተፈራረመን ባለሃብት የተሰጠዉ የኮንትራት ጊዜ እንዲያጥር ይደረጋል ማለት ምን ማለት ነዉ? የባለስልጣኑ አባባል ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፤ ህዝብን ለማዘናጋት ካልሆነ በስተቀር።” ብለዋል።

________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide