በ2011ዓ/ም የመን የገቡት ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ቁጥር 65ሺህ መሆኑ ታወቀ

መጋቢት ፳፰ (ሃይ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በየመን ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ከፍተኛ ችግር፤ እስራትና እንግልት እየደረሰባቸዉ መሆናቸዉን የዘገበዉ የመን ታይምስ ጋዜጣ የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኛ ከፍተኛ ኮሚሽነርን በመጥቀስ እንደገለፀዉ እኤአ በ20110 የመን የገቡት ስደተኞች ቁጥር 34ሺህ 422 ሲሆን በ2011 ይኸዉ ቁጥር ወደ 65ሺህ ከፍ ማለቱን አመልክቷል። በ2010 ከገቡት መካከል 616 ሰዎች እስካሁን የት እንደደረሱ የማይታወቅ ተገልጿል።  

የየመን መንግስት ወታደሮች ህገወጥ ናቸዉ የሚሏቸዉን ስደተኞች በቁጥጥር ስር እንደሚያዉሉ፤ እንደሚደበድቧቸዉና እንደሚያሰቃዩዋቸዉ በመግለፅ ቁጥራቸዉ ከ220 በላይ የሆኑ ኢትዮጵያዉያን በአንድ ክፍል ዉስጥ መታሰራቸዉንና በቀን አንድ ጊዜ ብቻ  ምግብ እንደሚያገኙ ለማወቅ ተችሏል።

ኢትዮጵያዉያን እስረኞች በሰንአ እንዲሁም በባብ አልመንደብ የባህር ወሽመጥ አካባቢ በምትገኘዉ ካራዝ በተባለች የጠረፍ አካባቢ በሚገኝ እስር ቤት ዉስጥ በሚገኝ የአፍሪቃዉያን እስር ቤት ዉስጥ እንደሚገኙ ታዉቋል።
የየመን የፀጥታ ሃይሎች ከሚያደርሱባቸዉ ወከባ የሚድኑት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የመታወቂያ ካርድ የያዙት ብቻ ሲሆኑ እነሱም ቢሆኑ ወደሌላ ሶስተኛ አገር እንዲሰፍሩ የሚጠሩበት እድል እጅግ የጠበበ በመሆኑ ብዙዎቹ እዚያዉ የመን ዉስጥ በችግር ዉስጥ እንደሚገኙና የአንዳንዶቹም የመታወቂያ ካርድ እንዳይታደስ የሚታገድ መሆኑን የዜና ምንጩ ገልጿል። 

በሌላ ዜና የየመን የአገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ባለፈዉ ወር በገለፀዉ መሰረት ሃጃህ በተባለዉ በአገሪቱ የሰሜን ግዛት ዉስጥ በሳዉዲ አረቢያ ድንበር አካባቢ ኢትዮጵያዉያንን ጨምሮ ቁጥራቸዉ 170 የሚሆኑ ህገወጥ ስደተኞችን ገንዘብ እንዲከፍሏቸዉ በመኖሪያ ቤታቸዉ አግተዉ ይዘዉ ያሰቃዩዋቸዉ የነበሩ ሁለት የታጣቂ ቡድኖች በመንግስት ቁጥጥር ስር መዋላቸዉ ተገልጿል። ከታገቱትት እስረኛ ስደተኞች መካከል 10 ሴቶች፤ 50 ህፃናትና 19 አቅመ ደካማ አዛዉንቶች እንደሚገኙባቸዉ ታዉቋል።

________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide