(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 20/2010) ከአራተኛ ፎቅ ሊወረወር የነበረውን ሕጻን ሕይወት የታደገው ማሊያዊ የፈረንሳይ ዜግነት አገኘ
በአካባቢው ሰው ተሰብስቦ የደረሰው ማሊያዊው ወጣት የሕጻኑን ሁኔታ ሲያይ ጊዜም አላባከነም አራቱን ፎቅ በፍጥነት በመውጣት የሕጻኑን ሕይወት ታድጎታል ብሏል የቢቢሲ ዘገባ።
የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ የሳበው ማሊያዊው ማሞዱ ጋሳማ የተባለው ወጣት ከፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም ምስጋና ተችሮታል።
በኤልሴ ቤተመንግስት በክብር ጠርተው ጋሳማን ያናገሩት ማክሮን ይህ ወጣት የትውልደ ፈረንሳዊ ዜግነት ይገባዋል ሲሉም ተናግረዋል።
በግላቸው ምስጋናቸውን የቸሩት ማክሮን የጀግና ሜዳሊያም ለማሞዱ ጋሳማ አበርክተውለታል።
ማሞዱ ለፕሬዝዳንቱ በማሰብ ጊዜ ማጥፋት አልፈለኩም መንገዱን በሩጫ አቋረጥኩ በቀጥታ ወደ ሕጽእኑ ነው የተወረወርኩት አዳንኩትም ሲል ነግሯቸዋል።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ማክሮን ለማሞዱ በእሳት አደጋ መከላከል ብርጌድ ውስጥም ተሳታፊ እንዲሆን ጥያቄ አቅርበውለታል።
ማሞዱ ከሃገሩ ማሊ በጀልባ ተሳፍሮ አስቸጋሪውን የሜዲትራኒያን ባህር አቋርጦ የፈረንሳይን ምድር የረገጠው ባለፈው አመት ነበር።