የሕወሃት አገዛዝ የ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር እርዳታ ጠየቀ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 13/2010) በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ለእለት የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር እርዳታ መጠየቁ ተነገረ።

ፋይል

እርዳታው የተጠየቀው 8 ሚሊየን ለሚጠጉ የድርቅ ተጎጂዎች ድጋፍ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት አስታውቋል።

በግጭትና በድርቅ ከተጎዱ ኢትዮጵያውያን መካከል 2 ነጥብ 4 ሚሊየን የሚሆኑት አርብቶ አደሮች ናቸው ተብሏል።

በኢትዮጵያ ባለፉት 3 አመታት ከተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ባሻገር በድርቅ ሳቢያ የተጠቁት 8 ሚሊየን ያህል ናቸው።

ፖለቲካዊ ቀውሱ በማየሉና በሃገሪቱ በተፈጠረው አለመረጋጋት ምክንያት ግን የድርቅ ሰለባዎቹ ተዘንግተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ አሁና ኢዚያክ አናዋ ለአሜሪካ ድምጽ የእንግሊዘኛው ክፍል እንደገለጹት በድርቅ ከተጎዱት መካከል 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሕጻናት በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ናቸው።

በተለይ ደግሞ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው 3 መቶ ሺ ሕጻናት በአጣዳፊ ችግር ላይ እንደሚገኙ የስራ ሃላፊው ገልጸዋል።

እናም ለተጎጂዎቹ በፍጥነት ካልተደረሰላቸው አደገኛ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት አስጠንቅቋል።

ይህም በመሆኑ የኢትዮጵያው አገዛዝ ችግሩን በራሱ መንገድ እፈታለሁ ሲል ቢቆይም አሁን ግን የድርቅ አደጋውን ብቻዬን መቋቋም አልችልም ብሏል።

በዚሁም መሰረት የኢትዮጵያው አገዛዝ የ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር እርዳታ መጠየቁ ተንግሯል።

እርዳታውን ለተጎጂዎች ለማድረስ የተባበሩት መንግስታት ቁጥጥር ካላደረገ የውጭ ምንዛሪውን ለሌላ ተግባር አገዛዙ እንዳይጠቀምበት ጥንቃቄ እንዲደረግ የረድኤት ሰራተኞች ያስጠነቅቃሉ።