(ኢሳት ዜና–ሕዳር 19/2010) የሕወሃትን አገዛዝ የሚያወግዙ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ተጠናክረው መቀጠላቸው ተነገረ።
የሃሮማያና የጅማ ዩኒቨርስቲ ተመሪዎች በተቃውሞ ላይ ናቸው።
35ሺ የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ግቢያቸውን ለቀው ሲወጡ የጅማዎቹ ደግሞ ከግቢያቸው እንዳይወጡ ታግተዋል።
በጋሞጎፋ ዞን ሳውላ፣አወዳይ እንዲሁም በወለጋ ሕዝባዊ ተቃውሞው እንደገና ተቀጣጥሏል።
በኢትዮጵያ የሕወሃትን የ26 አመታት አገዛዝ ለማክተም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚካሄደው ተቃውሞ እንደቀጠለ ይገኛል።
በጋሞጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ በግብር የተንገሸገሸው ነዋሪ የገቢዎችና ጉምሩክ ጽህፈት ቤትን ቅዳሜ ሕዳር 16/2010 ለሊቱን ሲያቃጥል አድሯል።
የሳውላ ከተማ ነዋሪዎች የሕወሃት አገዛዝ ወገኖቻችንን ለሚገልበት ጥይት መግዣ ግብር አንከፍልም ሲሉ ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ነዋሪዎቹ ከኦሮሚያ ቄሮና ከአማራ ፋኖዎች ጋር እንቆማለን ሲሉም ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ተቃውሞውን ተከትሎም ካለፈው እሁድ ጀምሮ የሳውላ ከተማ ወጣቶች እየታፈሱ መሆናቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ወጣቶቹ ግን ለአገዛዙ ማስፈራሪያዎች አንገብርም ይላሉ።
መልኩን እየቀያየረ አገዛዙን እያስጨነቀ ያለው ሕዝባዊ ተቃውሞ የዩኒቨርስቲ ግቢዎችንም እያሳተፈ መሆኑ ተነግሯል።
ለሕዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ሃይልን እየተጠቀመ ያለው የሕወሃት አገዛዝ የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ 35ሺ ተማሪዎችንም ከግቢያቸው ለቀው እንዲወጡ አስገድዷል።
ተማሪዎቹ በአባገዳዎች የተገባላቸው ቃል ባለመፈጸሙ ምክንያት ግቢውን ለቀው መውጣታቸው ነው የተነገረው።
የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዳይሄዱ በመከላከያና ፌደራል ፖሊሶች ታግደዋል።
ተማሪዎቹ በግቢያቸው ውስጥ እንደ እስረኛ ታግተው እንደሚገኙ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በሀረር ከተማ በ4ኛና ሜንሽን ትምህርት ቤት አካባቢም የተቃውሞ ሰልፍ በመደረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።
በአወዳይ ደግሞ የከተማው ሕዝብ አውራጎዳናዎችን በማጨናነቅ አገዛዙን እየተቃወመ መሆኑ ነው የተነገረው።
በወለጋ፣መንዲና ቢግ ከተሞችም ሕዝባዊ አመጹ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ጥያቄያቸው ደግሞ ጅምላ ግድያ የሚፈጽመው የመከላከያ ሰራዊት ከተማችንን ለቆ ይውጣ የሚል ነው።